በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት ሰላሙ የተረጋጋ ክልል ለመፍጠርና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በላቀ ትጋት ይሰራል -አቶ ይርጋ ሲሳይ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት ሰላሙ የተረጋጋ ክልል ለመፍጠርና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በላቀ ትጋት ይሰራል -አቶ ይርጋ ሲሳይ
ባህር ዳር፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት የተረጋጋ ሰላም በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በላቀ ትጋት እንደሚከናወኑ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የርዕሰ መስተዳደሩ የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለፁ።
"የዛሬ ትጋት፤ የነገ ትሩፋት" በሚል መሪ ሃሳብ 'የነገ ቀን' በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።
አቶ ይርጋ ሲሳይ እንዳሉት፤ በክልሉ በአዲሱ ዓመት የተገኘውን ሰላም አፅንቶ ለማዝለቅና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
''በአዲሱ ዓመት በአዲስ ተነሳሽነትና ጉልበት ሁላችንም ነገን አስበንና አቅደን መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ የልማት ስራዎችን ማከናወን ይገባል'' ብለዋል።
''ለዚህም ያሉንን መልካም ባህሎች፣ እሴቶች፣ ታሪኮችና ቅርሶችን በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው'' ሲሉም ገልፀዋል።
በአዲሱ ዓመት ሰላሙ የተረጋጋ ክልል ከመፍጠር ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለው አመራር፣ ባለሙያና መላ ህዝቡ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ በማድረግ ለፈጠራና ቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነ፣ በምክንያት የሚያምን ትውልድ በመገንባት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፤ ''በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን የነገን ቀን ስናከብር የኢትዮጵያን ብሩህ ነገ ቅርብ መሆኑን በማስገንዘብ ነው'' ብለዋል።
በተለይ ሴቶች፣ ህፃናትና አካል ጉዳተኞች ለችግር እንዳይጋለጡ ሁሉም በጋራ መረባረብ እንዳለበትም አመልክተዋል።
''በአዲሱ ዓመት ወጣቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በንቃት እንዲያከናውኑ በማስቻል መሆን አለብት'' ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ዘሪሁን ፍቅሩ ናቸው።
በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንም አስታውሰዋል።
"የዛሬ ትጋት፤ የነገ ትሩፋት" በሚል መሪ ሃሳብ የነገ ቀን በባህር ዳር ከተማ የክልሉና የከተማ አስተዳደር አመራር አባላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውሏል።