የኢትዮጵያ ነገ የተሻለ እንዲሆን እየተጋን ነው - የሃዋሳ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ነገ የተሻለ እንዲሆን እየተጋን ነው - የሃዋሳ ከተማ ወጣቶች
ሃዋሳ ጳጉሜን 5/2016 (ኢዜአ):- በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ በመሆን የኢትዮጵያ ነገ የተሻለ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የሃዋሳ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
በሲዳማ ክልል የጳጉሜን 5 የነገ ቀን በእግር ጉዞና በፓናል ውይይት በሃዋሳ ከተማ ተከብሯል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከሃዋሳ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ወጣቶችና ታዳጊዎች እንዲሁም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
ወጣት የአምላክስራ ሳሙኤል ነገ ብሩህ እንዲሆን ውጤታማ በመሆንና ሳንነጣጠል አንድ ሆነን መጓዝ ይጠበቅብናል ብላለች።
ለኢትዮጵያ ብሩህ መሆን የሚጠበቅብንን እንወጣለን ያለችው ወጣቷ የአምላክስራ ሀገ ለሀገሬ የተሻለ ዜጋ ለመሆን እሰራለሁ ስትል ገልጻለች።
ወጣት ዲቦራ ማቲ በበኩሏ ያለንን አቅም ተጠቅመን ሀገራችን ነገዋ ብሩህ እንዲሆን እንደምትሰራ ተናግራለች።
ኢትዮጵያ ያላትን ብዙ ሀብት በመጠቀም ለለውጥ መትጋት እንደሚገባም አመልክታለች።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት አገኘሁ አክሊሉ እንዳለው ለሀገር ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ወጣቱ የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት።
በስራ ላይ ያለንን አመለካከት በመቀየር እርስ በእርስ በመማማርና ስራ ፈጠራ ላይ በማተኮር ነገን ብሩህ ማድረግ ይገባል ብሏል።
የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሩ ነገን ለክልላችን ብሩህ ተስፋ የሚሆኑ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ወጣቱ ሀገርንና የተገኙትን ለውጦች ለማስቀጠል ከማንም በላይ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደስታ ለገሰ የክልሉ ወጣት ሰላምን ለማስጠበቅና ልማትን ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው ገልጸዋል።