ብልፅግና ፓርቲ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግናና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል- አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግናና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል- አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ በ2017 የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ብልፅግናና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ለመላው ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት የአዲስ ዓመት መልዕክት 2017 ዓ.ም የሰላም፣ የደስታ የፍቅር፣ የጤናና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም በአገር በቀል እሳቤዎች በመመራት ቃልን በተግባር ማረጋገጥ ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በደም የተከበረውን ነጻነት በላብ ለማጽናት የሚያስችሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ የማሳደግ ሥራዎች መከናናቸውን አመልክተዋል።
በተጠናቀቀው ዓመት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፤ ሰው ተኮር በተለይም ድሃ ተኮር የሆኑ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የከተማ ልማቶች መተግበራቸውንም አንስተዋል።
አዲስ አበባን ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ መዲናነት የምትመጥን እንድትሆን የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውንም ጠቁመዋል።
ልማትን በሚያሳልጥና አገልግሎት አሰጣጥን በሚያዘመን መልኩ አገራዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መሻሻሉንም ነው ያነሱት።
እንዲሁም ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት በውጤታማነት መገንባታቸውንም ጠቁመዋል።
የ2017 ዓ.ም ባለፉት ዓመታት ያስመዘገብናቸውን እምርታዎች፣ የህዝቡን የላቀ ተጠቃሚነት በሚያረጋገጥ አኳኋን ይበልጥ አስፍተን የምንሄድበት ዓመት ይሆናል ብለዋል።
አዲሱ ዓመት በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን ለማፅናት፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናና ውጤታማነትን በማረጋገጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ለማስከበር በትጋት የሚሰራበት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎችን ከመላው ሕዝብ ጋር በመሆን በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ሕዝቡም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረቡት አቶ አደም አዲሱ ዓመት በተስፋ፣ በአዲስ መንፈስ፣ የልብ መሻታችንን እውን የሚሆንበትና የስኬት ዓመት እንዲሆንም ተመኝተዋል።