ቀጥታ፡

በ2016 ዓ.ም የተከናወኑ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የትውልዱ አንድነት ማሳያና የኩራት ምንጭ ናቸው-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦በ2016 ዓ.ም የተከናወኑ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የዛሬውን ትውልድ የአንድነት ውጤት የሚያሳዩና የነገን ትውልድ የሚያኮሩ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎቸ ገለጹ።

ኢትዮጵያውያን አሮጌውን 2016 ዓ.ም በፈተና እና በስኬት ሸኝተው አዲሱን 2017 ዓ.ም በአዲስ ተስፋ ሊቀበሉ ሰዓታት ብቻ ቀርተዋል።

የተጠናቀቀው ዓመት እንደ ሀገር በተለያዩ የልማት መስኮች ስኬት የተመዘገበበት ነው የሚሉት የመዲናዋ ነዋሪዎች፥ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ከሰራን ምንም ነገር ከማሳካት የሚያግደን ነገር  እንደሌለ በዓመቱ አይተናል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ተጀምረው በዚህ ዓመት ወደ አዲስ የስኬት ምዕራፍ የገቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ተስፋ ወደሚጨበጥ ውጤት እየቀየሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አቶ ዳዊት ገነነ የኢትዮጵያውያን የህብረት ትጋታቸው ህያው ምስክር የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግድብ በተጠናቀቀው ዓመት ወደ አዲስ ብርሃን መፈንጠቁን አንስተዋል።

በተመሳሳይ በዓመቱ በገበታ ለሀገርና ለትውልድ የተከናወኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ ትውልድ ቋሚ ሀብትና ውርስ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመዲናዋ በዚሁ ዓመት የተጀመረው የኮሪደር ልማት እና ላለፉት ዓመታት  እየተተገበረ የሚገኘው አረንጓዴ አሻራ ተጨባጭ ውጤት ከማሳየታቸውም ባለፈ የነገዋን ኢትዮጵያ ጉዞ ብሩህ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ውብእሸት ወልደሚካኤል በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በህብረት ለአንድ ዓላማ ከተነሳን ውጤታማ መሆን እንደምንችል በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ማሳያዎች ናቸው ይላሉ። 

በፕሮጀክቶቹ ላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከመንግስታዊ አካል እስከ ተፎካካሪ ፓርትዎች አሻራቸውን ያኖሩባቸው መሆናቸው የኢትዮጵያውያንን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ ያደርጋቸዋል ብለዋል።


 

"በ2016 ዓ.ም ለስኬት የበቁ ፕሮጀክቶች ከተባበርን የማንወጣው ተራራ እንደሌለ ያየንባቸው ናቸው" ያሉት ደሞ አቶ ከድሮ ቃስዮ ናቸው።

ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በጋራ ጥረት ማሳካት ኢትዮጵያን በውርብ ጊዜ ከበለጸጉ ሀገራት በማሰለፍ የአፍሪካውያን ተምሳሌት ለማድረግ እንደሚያስችልም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

በመሆኑም በአዲሱ ዓመት በመካከላችን ያሉ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የልማት ስራዎችን በህብረት ለማሳካት መትጋት አለብን ብለዋል።

በቀጣይ በእቅድ የተያዙና የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት አንድነታችንን አጠናክረን አንቀጥላለን ያሉት ነዋሪዎቹ አዲሱ ዓመት የሰላምና ተስፋ ወደ ውጤት የሚቀየርበት እንዲሆንም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም