ቀጥታ፡

መጪውን አዲስ ዓመት ስናከብር ለአገር ሰላምና እድገት በመስራትና እርስ በርስ መረዳዳትን በማጠናከር ሊሆን ይገባል-የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦መጪውን አዲስ አመት ስናከብር ለአገር ሰላምና እድገት በመስራትና እርስበርስ መረዳዳትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።   

የሃይማኖት አባቶቹ መጪውን አዲስ ዓመት አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የክፋትም ሆነ የደግነት መነሻ ውስጣዊ አዕምሮን ማደስ ያስፈልጋል ብለዋል።

አዕምሮን በማደስ በአዲሱ አመት አገራችንን እናድስ ያሉት ፓትሪያሪኩ አዲሱ ዘመን በሃይማኖት መንፈስ ግጭትን በውይይት፣ መለያየትን በአንድነት፣ አለመግባባትን በዕርቅ ፈተን በመታደስ ማህበረሰብን ለመገንባት ጥረት እናድርግ ብለዋል። 

   

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ኢትዮጵያ የተለያዩ የሃይማኖቶች ተከታዮች  በሰላምና በፍቅር ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት አገር መሆኗን  በመጥቀስ ሁሉም ይህንን ተቻችሎ የመኖር ልምዱን  አጠናክሮ  መቀጥል  እንደሚገባው ተናግረዋል ።

ሁሉም አዲሱን አመት እርቅና ሰላም በማውረድ ለአገር ልማትና ዕድገት መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።

አዲሱ አመት የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ዘመን እንዲሆን በዓሉን  በመተባበርና በመረዳዳት ማሳለፍ  አለብን  ብለዋል።  


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ በበኩላቸው በአዲሱ ዓመት ለለውጥ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አዲሱን ዓመት ለአገር ሰላምና እድገት የምንሰራበትና የተቸገሩት የምናግዝበት  የአንድነት፣ የይቅርታና የምህረት ሰላም የሰፈነበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ አዲሱ ዘመን ከቤተሰብ አንስቶ በአገር ደረጃ ለሰላም የምንጸልይበትና የምንተገብርበት ዘመን እንዲሆንልን ተመኝተዋል።

በአዲሱ አመት እርስ በእርስ በመከባበርና በትጋት በመስራት ሰላም እንዲሰፍን መንፈሳዊና አገራዊ ኃላፊነትን መወጣት ይገባልም ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም