ዲፕሎማሲያችን በኢትዮጵያ የአብሮነት እሴት የዳበረ ነው - አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ዲፕሎማሲያችን በኢትዮጵያ የአብሮነት እሴት የዳበረ ነው - አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በአብሮነት እሴት የዳበረና በዓለም አቀፍ አውዶች ጭምር ብዝኃ ማኅበረሰብን ትኩረት ያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ ዓመት አስመልክቶ ለሚያሳድጋቸው ሕፃናትና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች የማዕድ ማጋራትና የአዲስ ዓመት ሥጦታ አበርክቷል።
በመርኃ ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ጊዜ፤ ተቋሙ ከዲፕሎማሲያዊ ሥራ ባሻገር በማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ተቋሙ የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት የራሱን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ገልጸው በዚህም 33 የነገ አገር ተረካቢ ሕፃናትን እየተንከባከበ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም ለሚያሳድጋቸው ለእነዚህ ሕፃናትና ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለሆኑ ሠራተኞች የማዕድ ማጋራትና የአዲስ ዓመት ሥጦታ አበርክቷል ብለዋል።
የአገሪቱ ዲፕሎማሲ በኢትዮጵያ በአብሮነት እሴት የዳበረ ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ አውዶች ድረስ ትኩረቱን በብዙኃን ማኅበረሰብ ክፍል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተቋሙ እየተከናወነ ያለው የበጎ አድራጎት ተግባር ዲፕሎማሲያችን በሰብዓዊ ተግባራት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ማመላከቻ ነው ሲሉም አምባሳደር ታዬ አብራርተዋል።
መጪው አዲስ አመት በመላው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ ሕፃናት አዲስ የተስፋና የድል ምዕራፍ የሚጀመርበት ዘምን እንዲሆን መዕልካም ምኝታቸውን ተመኝተዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች ለተደረገላቸው የአዲስ ዓመት ሥጦታ ምስጋና አቅርበዋል።