በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አዲስ መመሪያ ወደ ሥራ ሊገባ ነው

 አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5 /2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ፣ በትራፊክ ግጭት ሳቢያ የሚከተለውን ሕይወት መጥፋት ለመታደግና የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ  የሚሰራ አዲስ መመሪያ ወደ ሥራ ሊገባ ነው። 

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን በመዲናዋ በሥራ መግቢያና መውጫ ሠዓት ላይ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ፣ በትራፊክ ግጭት ሳቢያ የሚከተለውን ሕይወት መጥፋት ለመታደግ ብሎም የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ አዲስ መመሪያ አውጥቷል።

የጭነት፣  የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችንና መሰል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመወሰን በወጣው መመሪያ ቁጥር 149/2016 በተመለከተ ዛሬ ባለሥልጣኑ መግለጫ ሰጥቷል።  

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አማረ ታረቀኝ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በከተማው የጭነት፣ ማሽነሪዎችና መሰል ተሸከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ ሥራ የዋለው መመሪያ ቁጥር 38/2013 ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ያስከተለ ነበር ብለዋል።

በመመሪያው የተጣለው ሰዓት ገደብ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከጭነት ተሽከርካሪ ባለቤቶች፣ ግንባታ የሚያካሂዱ ድርጅቶችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች መመሪያው በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መቆየቱን ሲነሳ ቆይቷል ነው ያሉት። 

በመሆኑም የትራፊክ መጨናነቁን የሚቀንስና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ ለማሳለጥ መመሪያውን ማሻሻልና አዲስ መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተከትሎ መመሪያ ቁጥር 149/2016 መዘጋጀቱን አብራርተዋል። 

መመሪያው ከመስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

በዚህም ማንኛውም የጭነት ማመላለሻ ተሸከርካሪና የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት እስከ 3፡00 ሰዓትና ከሰዓት በኋላ ከ10፡30 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ከተማ ውስጥ መግባትም  ሆነ  በከተማ  ውስጥ መንቀሳቀስ፣ ጭነት መጫንም ሆነ ማራገፍ እንዲሁም በዋና ዋና ትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ መቆም የተከለከለ መሆኑን ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ገደቡ እሁድና የበዓል ቀናትን እንደማይጨምር አንስተዋል። 

የመመሪያው ተፈጻሚነት ወሰንም የከተማ ውስጥ የሚገቡ፣ በሚንቀሳቀሱ እንዲሁም አቋርጠው በሚያልፉ ከ1 ቶን በላይ ወይም ከ10 ኩንታል በላይ የመጫን አቅም የላቸው የተለያዩ የፈሳሽና የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎችና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም አመላክተዋል።

በከተማው ውስጥ የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው ዋና ዋና  መንገዶች ዳር መቆምም ይከለክላል ብለዋል። 

ተሽከርካሪዎቹ ወደ ከተማው በመግባትና በመውጣት ላይ ሳሉ ሠዓቱ ከደረሰባቸው ከከተማው ዋና መንገድ ወጣ ብሎ የትራፊክ እንቅስቃሴውን በማያውክ መልኩ መቆም እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል። 

እነዚህ ተሽከርካሪዎች በተከለከለው ሰዓት ላይ ወደ ከተማ ውስጥ በመግባትም ሆነ በመውጣት ላይ ሳሉ  እንዲሁም  በዋና ዋና መንገዶች ላይ ቆመው ከተገኙ 10 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው ገልጸዋል። 

በተከለከለው ሰዓት በዋና ዋና መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ፣ ጭነት የሚጭኑና የሚያራግፉ ከተገኙ አስከ 20 ሺህ ብር ይቀጣሉም ነው ያሉት። 

ይህ መመሪያ የፀጥታ ሥራ የሚያከናውኑና ሰሌዳቸው በአገር መከላከያ ወይም በፖሊስ የተመዘገበ ከባድና ቀላል የጭነት ተሽከርካሪዎችን፣ የድንገተኛ አደጋ ተሽከርካሪ ተብሎ የተለዩ ከባድና ቀላል ጭነት ተሽከርካሪዎችና ነዳጅ የሚያመላልሱ ቦቴዎችን እንደማያካትት ጠቁመዋል። 

መመሪያውን ተፈጻሚ ለማድረግ ባለሥልጣኑ በከተማው መግቢያ በሮች ላይ ጊዜ ገደቡን የሚገልጹ መረጃ በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም