በአዲሱ ዓመት ከተረጂነት ለመላቀቅና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት ከተረጂነት ለመላቀቅና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ
ጅግጅጋ ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦ በአዲሱ ዓመት ከተረጂነት ለመላቀቅና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ የስንዴና የሩዝ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ገለጹ።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ አዲሱን የ2017 ዓመት አስመልክተው ለመላው የክልሉ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አዲስ ዓመት አስመልክተው በጽህፈት ቤታቸው ባስተላለፉት "የእንኳን አደረሳችሁ" መልዕክት፤ በተጠናቀቀው ዓመት እንደ ሀገር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ የተካሄደበት እና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ የሆነበት ዓመት እንደነበረ አንስተዋል።
"በዓመቱ ከተሞቻችንን ለማዘመን ከፍተኛ ጥረት የጀመርንበት ነው" ያሉት አቶ ሙስጠፌ፤ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ መልካም ጅምሮች የታዩበት ዘመን መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም በተጠናቀቀው ዓመት የክልሉን ህዝብ ከተረጂነት ለማላቀቅና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ የስንዴና ሩዝ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
አክለውም የትምህርት ጥራት ለማሻሻል እና በገቢ አሰባሰብ እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ክልሉ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸው፤ እነዚህ ስራዎች በአዲሱ ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
በክልሉ የተገኘውን ሰላምና መረጋጋት በማጠናከር በአሸባሪ ሀይሎች ሊፈጸሙ የሚችሉ ትንኮሳዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የፀጥታ መዋቀሩ ከህዝብ ጋር የሚያደርገው ትብብርም በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የአንድነት፣ የሰላም፣ የደስታና የስኬት ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።