ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመስጠት የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ይገባል - አቶ አወሉ አብዲ - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመስጠት የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ይገባል - አቶ አወሉ አብዲ

አዳማ ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦የተቀናጀና ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመስጠት የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለፁ ።
በአዳማ ከተማ አስተዳደር የተገነባውና የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሁለገብ ህንፃ በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አወሉ አብዲ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ሁለገብ ህንጻው የከተማ አስተዳደሩን የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ወደ ላቀ ከፍታ ያሳድገዋል።
ህንፃው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀና የአገልግሎት አሰጣጡን በዘመነ መልኩ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ጥራት ያለውን የአስተዳደር ህንፃ ከመገንባት ባለፈ "ፕሮጄክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ አጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቁ እያስቻልን ነው" ያሉት አቶ አወሉ፤ ለዚህም የአዳማ ከተማ አስተዳደር ኮምፕሌክስ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጣችን በቀጥታ የነዋሪው ቤት ድረስ ለማድረግ ዲጂታላይዜሽንና ቴክኖሎጂ ላይ በትኩረት በመስራት በአዲሱ ዓመት የህዝቡን እርካታ ያረጋገጠ አገልግሎት መስጠት አለብን ብለዋል።
ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለፈ በከተሞች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና በክህሎት ላይ ያተኮረ ሙያተኞችና የሰው ሃይል በብዛት ማፍራት ሌላው የክልሉ መንግሥት ትኩረት ነው ያሉት።
በዚህም አዳማ ከተማ የጀመረችውን የስማርት አዳማ ፕሮጄክት፣ የኢንተርፕሩነር ልማት፣ የጎጆ ኢንዱስትሪና የኮሪደር ልማቶችን በጥራት ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የከተማዋን የልማትና ዕድገት ቀጣይነት የሚወስኑና የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
አዳማን ፅዱ፣ ወብና ለኑሮ አመች የሆነች ከተማ ለማድረግ በተለይም የወደፊት የዕድገት ደረጃዋን የሚመጥኑ ተቋማት ማኖር ትኩረት ካገኙ ጉዳዮች መሆናቸውን በማንሳት።
ህንጻው በ12 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና ከሶስት ሺህ በላይ ተሰብሳቢዎችን ማስተናገድ የሚችል ማዕከል፣ የስፖርት ማዘወተርያና የመዝናኛ ማዕከል፣ የኦሮሞ የባህል፣ አርቲና ቲያትር ማዕከል የያዘ መሆኑን አንስተዋል።
ህንፃው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀና የኦንላይን አገልግሎት፣ የአይሲቲ መሰረተ ልማት እንዲሁም የደህንነት ቴክኖሎጂዎችን ያሟላ መሆኑን አክለዋል።