የአሁኑ ትውልድ የቀደሙ አባቶችን አኩሪ ተጋድሎ በመመልከት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የራሱን አሻራ ማኖር ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የአሁኑ ትውልድ የቀደሙ አባቶችን አኩሪ ተጋድሎ በመመልከት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የራሱን አሻራ ማኖር ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2016 (ኢዜአ)፦ የአሁኑ ትውልድ የቀደሙ አባቶችን አኩሪ ተጋድሎ በመመልከት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የራሱን አሻራ ማኖር እንደሚጠበቅበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በድል በመወጣት ሉአላዊነቷንና ነጻነቷን አስከብራ የኖረች አገር ናት።
ልጆቿ ለነጻነቷ ባደረጉት ተጋድሎ ኢትዮጵያ የሚለው ስም በፈተና ሳይበገሩ የማለፍና እንቅፋቶችን ተሻግሮ ድል የማድረግ የክብር ስም መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ትውልድ የሚቀባበለው አሁንም አጽንተን የምንቀጥለው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን አገራቸው በጸና አገረ መንግሥት ግንባታ እንድትቀጥል በየዘመናቱ ውድ መስዋትነትን መክፈላቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ የቅኝ ግዛት መስፋፋትን በመፋለም ኢትዮጵያን የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መገለጫ የሆነች አገር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ያስመዘገቡት ድል ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ በአርዓያነት የሚወሰድ የእኩልነትና ነጻነት ምልክት መሆኑን አንስተዋል።
የጣሊያን ፋሺስቶች ዳግም በኢትዮጵያ ላይ በፈጸሙት ወረራ አርበኞች ያደረጉት ተጋድሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
ቅድመ አያቶቻችን የፈጸሙት አኩሪ ተጋድሎም ኢትዮጵያዊያን አሁን ላለንበት ሉዓላዊ ነፃነት ምቹ መደላድልና መሰረት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ነጻነትና ሉአላዊነት የሚጸናው የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አርአያ በመከተል የራሱን አኩሪ አሻራ ማኖር ሲችል መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ትውልዱ ብርታትና ጥንካሬውን ሁሉ ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ላይ በማዋል የኢትዮጵያን ክብር ማረጋገጥ ይገባዋል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም ቅድመ አያቶቹ ለኢትዮጵያ ክብር የከፈሉትን ዋጋ ታሳቢ በማድረግ ለተሟላ ሉዓላዊነት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተለይም ድኅነትን ድል ለመንሳት የተጀመሩ የልማት ተግባራትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩልም የሳይንስና ቴክኖሎጂ የጥበብ ትሩፋቶችን ለአገር ዕድገት፣ ለበጎ ዓላማና ለተሻለ የልማት ተጠቃሚነት ማዋል እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ብሔራዊ ክብሯ ላይ የሚቃጡ ጫናዎችን መቀልበስ የቻለች ጽኑ ሀገር መሆኗን ታሳቢ በማድረግ የአሁኑ ትወልድ የራሱን ደማቅ አሻራ በማኖር ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት የሚጠበቅበት መሆኑን አስገንዝበዋል።