ቀጥታ፡

ሕብረተሰቡ ለአዲሱ ዓመት ከእርድ የሚገኘውን ቆዳና ሌጦ በጥንቃቄ አዘጋጅቶ በወቅቱ ለገበያ እንዲያቀርብ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኢዜአ)፦ ለአዲሱ ዓመት ከሚፈጸም እርድ የሚገኘውን ቆዳና ሌጦ በጥንቃቄ በማዘጋጀትና በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

በአዲሱ ዓመት ሕብረተሰቡ እርድ ሲፈጽም ለቆዳና ሌጦ ጥራት ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ለራስም ሆነ ለአገር ጥቅም መሥራት እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በሰጠው መግለጫ ጠቁሟል።


 

የኢንስቲትዩቱ የቆዳ ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሚሻሞ ሞካሶ፤ የቆዳና ሌጦ ውጤቶች በሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ 

በበዓላት ወቅት በሚከናወን እርድ ለቆዳ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለመደረጉ ቆዳና ሌጦ ከጥቅም ውጭ እንደሚሆንና ሀብት እየባከነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሕብረተሰቡ ለአዲስ ዓመት እርድ ሲያከናውን ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ቆዳው ሲገፈፍ በቢላዋ እንዳይበሳ፣ እንዳይቆሽሽና እንዳይበሰብስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ ዳኛቸው አበበ የሚከናወኑ እርዶችን በባለሙያ የታገዙ በማድረግ የቆዳና ሌጦን ጥራት  ማስጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡


 

ቆዳና ሌጦን መሠረት በማድረግ የተቋቋሙ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ለበርካታ ዜጎች ስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመው የቆዳው ዘርፍ ተኪ ምርቶችን ከማምረት አንጻር ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮ-ሌዘር ኢንዱስትሪ /አሊኮ/ ቆዳ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ኤርሚያሥ ወሰኑ በበኩላቸው በአዲሱ ዓመት ከሚከናወን እርድ የሚገኘውን ቆዳና ሌጦ ለመሰብሰብ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለውን ቆዳና ሌጦ በጥንቃቄ በማረድ ለሚመለከተው አካል ማድረስ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በጋራ የመኖሪያ ቤቶች ከሚከናወኑ እርዶች የሚገኙ ቆዳና ሌጦዎችን ለመሰብሰብም ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የእርድ እንስሳትን በዱላ አለመምታት፣ የእርድ ቦታን ንፁህ ማድረግ እና ቆዳ ሲገፈፍ የተፈጥሮ መስመርን ተከትሎ መሰንዘር አስፈላጊ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡ 

በኢትዮጵያ የቆዳ ጥራትን ጠብቆ ለገበያ በማቅረብ ለአገር ጥቅም ከማዋል ባለፈ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ተብሏል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም