መንግስት አካል ጉዳተኞች በስፖርቱ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል -ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦መንግስት አካል ጉዳተኞች በስፖርቱ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

በ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑካን ቡድኑ ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎለታል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ አትሌቶች በፓራሊምፒክ ውድድር ከባለፉት ጊዜያት የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ስሟ በመልካም እንዲነሳ ስላደረጋችሁ ኮርተንባችኋል እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

መንግስት በስፖርት ፖሊሲው ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አካል ጉዳተኞች በስፖርቱ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ አንዱ መሆኑን ገልጸው ይህን የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

መንግስት በውድድሩ ተሳትፎ ላደረገውና አመርቂ ውጤት ላስመዘገበው የልዑካን ቡድን የእውቅናና ሽልማት እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል።

በ1500 ሜትር ሙሉ ለሙሉ የአይነ ስውር ምድብ (T-11) የራሷን የዓለም ክብረ ወሰን በማሻሻል የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ያየሽ ጌቴ ውድድሩ ፈታኝ ቢሆንም ጫናዎችን በመቋቋም ለማሸነፍ በመቻሏ ደስተኛ እንደሆነች ገልጻለች።


 

በቀጣይ በተለያዩ ርቀቶች በመወዳደር ኢትዮጵያን ለማስጠራት እቅድ እንዳላት ተናግራለች።

የአትሌት ያየሽ ጌቴ አሯሯጭና አሰልጣኝ ክንዱ ሲሳይ የወርቅ ሜዳሊያ መገኘቱንና የዓለም ክብረ ወሰን መሻሻሉ ድርብ ድል መሆኑን ገልጿል።

ለፖራሊምፒክ ስፖርት ትኩረት መስጠት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ውድድሩ ማሳያ መሆኑን አመልክቷል።

በ1500 ሜትር ጭላንጭል ውድድር(T-13) የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ እንደ ቡድን የተደረገው ዝግጅት ለውጤቱ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጻለች።

በሁለት ተከታታይ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት አዲስ ታሪክ በመስራቷና የኢትዮጵያን ስም ከፍ በማድረጓ ክብር ይሰማኛል ብላለች።

በ150ዐ ሜትር አይነ ስውራን ምድብ(T-11) የብር ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ይታያል ስለሺ በመጀመሪያ ተሳትፎው ባስመዘገበው ውጤት መደሰቱን ገልጾ አገሩን ወክሎ በመወዳደሩ ኩራት እንደተሰማው ተናግሯል።

በቀጣይ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አገሩን በመወከል የወርቅ ሜዳሊያ እንደሚገኝ ሙሉ እምነት አለኝ ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፖራሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ንጋቱ ሀብተማርያም ለውድድሩ ለሁለት ወራት ገደማ የተደረገው ዝግጅት ለውጤቱ መምጣት አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጿል።

በቀጣይ ውድድሮች ውጤታማ ለመሆን የተሳታፊ አትሌቶችና የውድድር አይነቶችን መጨመርና ለፓራሊምፒክ ስፖርት የበለጠ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

ከነሐሴ 22 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ በተካሄደው 17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ2 የወርቅና 1 የብር በድምሩ ሶስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም 44ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው ፓራሊምፒክ ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት እ.አ.አ በ2021 በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ካገኘችው አንድ የወርቅ ሜዳሊያ የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያ ቶኪዮ ላይ 56ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም