የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ በብልፅግና ጉዟችን ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል በፖሊሲዎቻችን እና በፍኖተ ብልጽግና እቅዳችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ በብልፅግና ጉዟችን ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል በፖሊሲዎቻችን እና በፍኖተ ብልጽግና እቅዳችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ በብልፅግና ጉዟችን ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል በፖሊሲዎቻችን እና በፍኖተ ብልጽግና እቅዳችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
በስነ ምግባር የታነፀ፣ ተስፋው ሙሉ እንደሆነ የሚያምን፣ ለወንድማማችነት እና እህትማማችነት ቦታ የሚሰጥ፣ የሰብዓዊነት አስተሳሰቡ የዳበረ፣ የሞራል ልዕልናው በልህቀት የተሞላ ትውልድ ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀጣይነት ይኖራት ዘንድ ታላቅ ህልምን በማንገብ ጉዟችንን ጀምረናል ብለዋል።
አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ይህም እውን ይሆን ዘንድ የትምህርት፣ የጤና፣ የከተማ ልማት እና የሌሎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችን የነገውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ እንዲሻሻሉ እንዲሁም በአዳዲስ ሀሳቦች የቀጣዩን ትውልድ ዘመን እንዲዋጁ ተደርጓል ሲሉም ገልጸዋል።
ለቴክኖሎጂ፣ ለዘመናዊነት፣ ለፈጠራ ሀሳቦች ቅርብ የሆነ በሀገር በቀል እሳቤዎች ተመርኩዞ ማህበረሰባዊ እድገትን የሚያረጋግጥ ትውልድን ለመቅረፅ የጀመርናቸው ስራዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል ብለዋል።
በዛሬው የጳጉሜን 5 የምናከብረው "የነገ ቀንም" የመደመር ትውልድ ብለን ስያሜ የሰጠነው ባለ ተስፋው ትውልድ ይበልጥ ሀገሩን እንዲወድ፣ በሀገሩ ተስፋ እንዳለው እንዲያስብ የምናደርግበት፣ አለንልህ ብለን ከጎኑ የምንቆምበት፣ ከስህተቶቻችን ተምረን ነገን ውብ አድርገን የተሻለች ሀገር እንደምናስረክበው ቃል የምንገባበት ነውና እንኳን አደረሳችሁ እንኳን አደረሰን ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።