የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጫና ውስጥ ሆነው ነገን ዛሬ የገነቡበት የህብረታቸው ተምሳሌታዊ ፕሮጀክት ነው-ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጫና ውስጥ ሆነው ነገን ዛሬ የገነቡበት የህብረታቸው ተምሳሌታዊ ፕሮጀክት ነው-ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጫና ውስጥ ሆነው ነገን ዛሬ የገነቡበት የህብረታቸው ተምሳሌታዊ ፕሮጀክት መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብዙ ውስብስብ ፈተናዎችን አልፎ የመጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ኢትዮጵያውያንም የጋራ ሃብታቸውና የአንድነታቸው አርማ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለኢዜአ እንዳሉት ግድቡ መላው ኢትዮጵያውያን ብዙ ዋጋ ከፍለው የገነቡት የወል ምልክት ነው።
የኢትዮጵያውያን የህብረት ተምሳሌት የሆነው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጠቃላይ የግንባታ ሂደት 96 ነጥብ 8 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከለውጡ በፊት በነበሩ የፖለቲካ ውሳኔዎች ፈተና ተጋርጦበት እንደነበር አስታውሰው ፥ መንግስት በፍጥነት የወሰዳቸው ርምጃዎች ለፕሮጀክቱ ዳግም ህይወት መዝራታቸውን ተናግረዋል።
የለውጡ መንግስት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከገጠመው ፈተና በማውጣት ወደ ግንባታ ሲሸጋገር ከሁሉም አቅጣጫ ጫናዎች በርትተውበት እንደነበር ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ በሲሚንቶ እና ኮንክሪት ብቻ የተገነባ አይደለም የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ፥ ግንባታውን ከዚህ ለማድረስ ኢትዮጵያውያን ትልቅ መስዋእትነት ከፍለዋል ብለዋል።
ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ጫፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደ አይናቸው ብሌን ለሚጠብቁት ፕሮጀክት ከገንዘብና ጉልበት አልፎ ውድ ህይወታቸውን ገብረውለታል ብለዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብን መገንባት ፍትሀዊና የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ በዓለም አደባባይ ድምፃቸውን አሰምተዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ፣መንግስት እና የጽጥታ አካላት በመቀናጀት የተከፈተውን ዘመቻ ተቋቁመው ለድል መብቃታቸውንም ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጫና ውስጥ ሆነው ነገን ዛሬ የገነቡበት የጋራ ትጋት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።