ፖሊስ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኮንትሮባንድ እቃ ከወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኮንትሮባንድ እቃ ከወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኮንትሮባንድ እቃ ከወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት ጋር በመሆን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ዕቃ መያዙን ነው ያስታወቀው፡፡
በዚህም ኮንትሮባንድ ጭኖ አዲስ አበባ ሊያሰራጭ ሲሞክር ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ ሹፌሩንና ረዳቱን እስከ ሙሉ የኮንትሮባንድ እቃው በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።
በቁጥጥር ስር የዋለው የኮንትሮባንድ ዕቃ በሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3- 79635 ኢ.ት ተሳቢ ተሽከርካሪ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን ሲጋራ፣ ልባሽ ጨርቅ (ቦንዳ) እና Appl car play ጭኖ መገኘቱን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገር ላይ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ህገወጥ ተግባር ለመከላከል ማህበረሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም እገዛ ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ፖሊስ ጥሪ አስተላልፏል።