በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 5/2016 (ኢዜአ)፦ በ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትና የዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ(ዶ/ር) እና የኮሚቴው አመራሮች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ከነሐሴ 22 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ በተካሄደው 17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ2 የወርቅና 1 የብር በድምሩ ሶስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት 44ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው ፓራሊምፒክ ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት እ.አ.አ በ2021 በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ካገኘችው አንድ የወርቅ ሜዳሊያ የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያ ቶኪዮ ላይ 56ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም