ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት በጀግንነት የሚያስከብር እና ታሪካዊ ጠላቶችን የሚያሳፍር ጠንካራ የሜካናይዝድ ጦር ተገንብቷል-ሜጀር ጀኔራል ከፍያለው አምዴ

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት በጀግንነት ማስቀጠል የሚችል እና ታሪካዊ ጠላቶችን የሚያሳፍር ጠንካራ የሜካናይዝድ ጦር መገንባቱን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሜካናይዝድ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ከፍያለው አምዴ ገለጹ።

አዛዡ ይህን ያሉት የዕዙን ዝግጁነት እና የአዲስ ዓመት ዋዜማን ምክንያት በማድረግ በዕዙ ማሰጠልኛ ማዕከል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።


 

ዕዙ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በሰው ኃይል፣ በስነ ልቦና እንዲሁም ዘመኑን በዋጁ ትጥቆች ራሱን በማደራጀት በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

ከተመሰረተ 74 ዓመታትን ያስቆጠረው የሜካናይዝድ ዕዝ የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ታራካዊ ጠላቶች በየዘመኑ የሞከሯቸውን ሀገር የማፍረስ ዕኩይ ሴራዎች  በማክሸፍ አኩሪ ገድል መፈፀሙን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሀገራችን ተፈጥሯዊ ሀብቷን ተጠቅማ እንዳትበለፅግ እና ህዝቧ በሰላም እንዳይኖር እስከ ወረራ ሙከራ የደረሰ ሴራ ሲያሴሩ መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ጠላቶቿን በየጊዜው የሀፍረት ካባ በማልበስ የሚመልሱ ጀግኖችን የታደለች በመሆኗ፥ የጠላት ሙከራዎች በሙሉ ከሽፈዋል ብለዋል።

አሁንም የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችን በመጠቀምና በተሳሳተ ግምገማ ኢትዮጵያን ለመተንኮስ ቀቢጸ ተስፋ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል።

ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና መላው ህዝቧ ከየትኛውም ኃይል የሚቃጣ ጥቃትን በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት የሀገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነትን እንደሚያስከብሩም አረጋግጠዋል።

የሜካናይዝድ ዕዙም በአንድ ጊዜ ብዙ ግዳጅ መፈፀም የሚያስችል  ጠንካራ ቁመና መገንባቱን ጠቁመው፤ ወደፊትም ከምንጊዜም በላይ ማሰልጠን እና ማዘጋጀት ይቀጥላል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም