በሀገር ላይ የሚቃጣ የትኛውንም ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ ቁመና ላይ እንገኛለን- የሜካናይዝድ ዕዝ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ላይ የሚቃጣ የትኛውንም ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ ቁመና ላይ እንገኛለን- የሜካናይዝድ ዕዝ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ የሀገር ክብርና ሉዓላዊነትን በአኩሪ ጀግንነት አስጠብቆ የቀጠለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሜካናይዝድ ዕዝ ዛሬም ዘመኑን በዋጀ አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የሜካናይዝድ ዕዝን የወታደራዊ ተልዕኮ ዝግጁነት እና የአዲስ ዓመት ዋዜማን አስመልክቶ በዕዙ ማሰልጠኛ ማዕከል የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተካሂደዋል።
በመርሐ ግብሩ የዕዙ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ከፍያለው አምዴን ጨምሮ የዕዙ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ታሪክ ከ1940ዎቹ መባቻ ጀምሮ መደራጀት የጀመረው የሜካናይዝድ ጦር ክፍል በረጅም ዘመን ታሪኩ የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር በማስጠበቅና በማስከበር አኩሪ ገድል ጽፏል።
በታሪኳ በየትኛውም ሀገር ላይ ወረራ ፈጽማ የማታውቀውና በርካታ የወረራ ሙከራዎች የተደረጉባት ኢትዮጵያ፥ ጠላቶቿን አሳፍራ በመለሰችበት አኩሪ ታሪኳ የሜካናይዝድ ጦሯ የወገን ኩራት፣ የጠላት መቅሰፍት በመሆን በርካታ ጀብዱዎችን ፈጽሟል።
የዛሬው የሜካናይዝድ ዕዝ ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ ራሱን ችሎ የተደራጀ፣ ዘመኑ የደረሰባቸውን ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች የታጠቀ እና በሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል የተገነባ የሀገር መከታ የጦር ክፍል ነው።
በአዲስ መልኩ በተደራጀው ሜካናይዝድ ዕዝ በተሟላ ትጥቅ የሀገርን ክብር የሚያስጠብቅ አስተማማኝ ቁመና ተፈጥሯል።
ዕዙ የቀጣናውን ተለዋዋጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የተሟላ ቁመና ያለው እና በሀገር ላይ የሚቃጣ ማንኛውም ጥቃት ማክሸፍና መመከት የሚያስችል ጠንካራ አቅም አለው።