በደሴ ህገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ገበያውን የማረጋጋቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ህገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ገበያውን የማረጋጋቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለጸ

ደሴ ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በአዲሱ በጀት ዓመት ጠንካራ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ገበያውን የማረጋጋቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል ፤የንግድ ቀንም ተከብሯል።
ለዘመን መለወጫ በዓልም ሽንኩርት፣ ቲማቲምና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ መምሪያው አመልክቷል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዮናስ እንዳለ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
በዚህም በ48 ሚሊዮን ብር በመመደብ ከ65 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ የአቅርቦት ክፍተትን በመሙላት የገበያውን የማረጋጋት ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በዓላትን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ እንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በማቅረብ እንዲሁ።
በአዲሱ በጀት ዓመትም ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ጠንካራ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ገበያውን የማረጋጋቱ ተግባር በልዩ ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በዚህም በ50 ሚሊዮን ብር በመመደብ ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማቅረብ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
እንዲሁም የእሁድ እና ጊዜያዊ ገበያዎችን ጭምር በማመቻቸት አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘትም ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።
ለዘመን መለወጫ በዓልም ሽንኩርት፣ ቲማቲምና የእንሰሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አበረታችና ተስፋ ሰጭ ውጤት በመገኘቱ ጅምላ አከፋፋዮችና ሌሎችም ነጋዴዎች ምርት በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት የሚያደርጉትን መልካም ጅምር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንታው ፈጠነ ፤ በክልሉ ገበያውን ለማረጋጋት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲሱ የበጀት ዓመት ህገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ገበያውን ለማረጋጋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመድረኩ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላትን ጨምሮ ምስጉን ነጋዴዎች የተሳተፉ ሲሆን የተሻለ ለሰሩ ባለሙያዎችና ነጋዴዎችም እውቅናና ሽልማት ተበርክቷል።