በሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ኅብረት በዘላቂ የሰላም ግንባታና በሌሎች የልማት ሥራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ኅብረት በዘላቂ የሰላም ግንባታና በሌሎች የልማት ሥራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦በሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ኅብረት በዘላቂ ሰላም ግንባታና በሌሎች የልማት ሥራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተመላከተ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን፤ የውስጥ አንድነት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል ዋነኞች ናቸው ብለዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በራሳችን አቅም ገንብተን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ አድርሰነዋል ብለዋል።
ግድቡ አሁን የደረሰበት የስኬት ደረጃ ፤ በጋራ መቆም ከተቻለ የተለያዩ ግዙፍ ውጥኖችን ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳይ ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ጠና ደዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው አንድነት በሥምምነት ይፀናል፤ ሥምምነት ደግሞ የማስተሳሰር ኃይል አለው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተግባብተንና ተስማምተን በአንድነት ወደ ሥራ በመግባታችን የመጣ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆማችን አቅም የፈጠርንበት፤ በሥምምነታችንም ውጤት ያገኘንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያንም በአድዋ ድልና በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳየነውን አንድነትና ኅብረት የአገርን ሉዓላዊነት ሊያስጠብቁ በሚችሉ ሁለንተናዊ የልማትና የሠላም ማጽናት ሥራዎች ላይ አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።
የአንድ አገር ሕልውናና እድገት የሚወሰነው በዜጎቿ ህብረት፣አንድነትና አብሮነት በመሆኑ ዜጎች ከራሳቸው የአገርን ፍላጎት ማስቀደም ይገባል ብለዋል ምሁራኑ።