ኢዜአ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በቋሚነት ለሚደግፋቸው ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በቋሚነት ለሚደግፋቸው ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የ2017 አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በቋሚነት ለሚደግፋችው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና ለበዓል መዋያ የሚውሉ የተለያዩ የፍጆታ ቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው የአዲስ ዓመት የስጦታ መሰጣጣት ባህልን ምክንያት በማድረግ ከተቋሙ ሰራተኞች ከተዋጣው ነው።
ለተማሪዎቹ የተደረገው የትምርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተማሪዎቹ ጠንክረው እንዲማሩ ለማበረታታት እንደሆነም ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
በኢዜአ የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ በበኩላቸው የተቋሙ ሰራተኞች በሚያደርጉት መዋጮ በቋሚነት ድጋፍ የሚያደርግላቸው ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በዛሬው እለትም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግም በአጠቃላይ በተቋሙ በቋሚነት ድጋፍ ለሚደረግላቸው 20 ተማሪዎች የትምህርትና የበዓል መዋያ የፍጆታ ሸቀጦችን ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
በድጋፉ ከተደረገው የመደበኛ የትምህርት ቁሳቁስ ባሻገር በ2016ዓ.ም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች አጋዥ መጽሐፍት እንደተበረከተላቸው ተናግረዋል።