ኢትዮጵያ ራዕይ ያላቸውና የሚተጉ የፈጠራ ወጣቶች ካሏት በአጭር ጊዜ መለወጥና ማደግ ትችላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ራዕይ ያላቸውና የሚተጉ የፈጠራ ወጣቶች ካሏት በአጭር ጊዜ መለወጥና ማደግ ትችላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ራዕይ ያላቸውና የሚተጉ የፈጠራ ወጣቶች ካሏት በአጭር ጊዜ ወለወጥና ማደግ ትችላለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የ2016 ዓ ም ሰመር ካምፕ ሰልጣኞች የምርቃት መርሐግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ የተጀመረው ሥራ ለነገ መልካም ፍሬ ዛሬ የሚዘራ ምርጥ ዘር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እየሰጠ ያለው ስልጠና ለኢትዮጵያ መፃኢ ትውልድ የተሻለ የፈጠራ ሰው መሆን ወሳኝ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች መንግሥት ለቴክኖሎጂ ትኩረት መስጠቱንና ለሥራቸው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ብለዋል።
ለአብነትም በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ቴክኖሎጂ አንዱ የዕድገት መሠረት ሆኖ በእቅድ እየተሠራበት መሆኑን ገልጸዋል።
ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለማዘመን ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና ስለሚጫወት ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
በቅርቡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዲጂታል ፊርማን በይፋ ማስጀመሩን ጠቅሰው፤ይህ በሀገር ልጆች የተሠራ እና ለቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ፋይዳው የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
በሀሰተኛ ማንነት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቀነስና ወጥ አሠራርን ለመተግበር ኢትዮጵያውያን ዲጂታል መታወቂያ እንዲኖራቸው የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
አሁን ላይ ለ10 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ምዝገባ የተደረገ ሲሆን፥ የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ለወጣቶችና ታዳጊዎች ጠቀሜታው የላቀ መሠረተ ልማት ነው ብለዋል።
የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ እውቀት ብቁ ወጣቶችን በማፍራት ለፈጠራና ለተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተጀመሩ የዲጂታል ሥራዎችም ለፈጠራ ሰዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ አንስተዋል።
አገራት በቴክኖሎጂ ያደጉት ለወጣቶችና ታዳጊዎች በሰጡት ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በትጋት ስኬታማ ፈጠራን የሚያከናውኑ ወጣቶች ካሏት፤ በቅርቡ ቴክኖሎጂን ከሚፈጥሩ አገራት ጎራ መሰለፍ እንደምትችልም አንስተዋል።
በመሆኑም ተማሪዎች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በፈጠራና በትጋት ለለውጥ ማዋልና መመራመር ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የእነዚህ ተስፈኛ ታዲጊ ወላጆችም ልጆቻቸውን በአግባቡ እየቀረፁ በመሆናቸው ሊኮሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ኢንስቲትዩቱ የተፈጠረለትን ዓላማ እያሳካ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዛሬ ተመራቂዎች ከራሳቸው ባለፈ ለብዙዎች የእንጀራ ምንጭ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፣ ለሁለት ወራት በቆየው ስልጠና ከመላ ሀገሪቱ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 200 ተማሪዎች ተከታትለዋል ብለዋል።
የዘንድሮው የሰመር ካምፕ ስልጠና ሰልጣኞች የቴክኖሎጂ ስብጥርን፣ ፈጠራና ችሎታን ያሳዩበት በግልና በቡድን ስኬታማ መሆንን በተግባር ያረጋገጡበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተማሪዎች በቀጣይ ጉዟቸው አዲስ ነገርን የማወቅ ሂደታቸው ላይ ፈተናዎች ለዕድገት እድል መሆኑን በመረዳት መትጋትና መሥራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።