ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶችን ሰጠ

ድሬዳዋ ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 10 ሚሊዮን ብር  የሚገመት የኤሌክትሮኒክስ እና የትምህርት መርጃ ቁሶችን አበረከተ።

85 ላፕቶፖች፣ 17 ራውተሮች፣  ስድስት ሺህ ደብተሮች እና 750 እስክሪብቶዎች ለቢሮው ከተደረጉት ድጋፎች መካከል ሲሆኑ አጠቃላይ ዋጋቸውም 10 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል።

ከንቲባ ከድር ጁሃር በዚሁ ወቅት እንዳሉት ድጋፉ የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ እና ዲጂታል የትምህርት አሰጣጥን ለማሳደግ ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸው፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

በተለይም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት በትምህርት መርጃ ቁሶች እጥረት ችግር  ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ ለማገዝም እንዲሁ።

የሰፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዘሪሁን በበኩላቸው ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ኩባንያው የራሱ ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል።

የኤሌክትሮኒክስ ቁሶቹ ተማሪዎች ዲጂታል የመማር ማስተማር ሂደትን በማዳበር ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል።

የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሃላፊው አረጋግጠዋል።

ድጋፉን የድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ የተረከቡ ሲሆን የተገኘው ደጋፍ ለ10 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ለአምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚከፋፈል መሆኑን በመርሃ ግብሩ ላይ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም