የኢትዮጵያን ስም በዓለም ከፍ አድርገው የሚያስጠሩ ቴክኖሎጂዎችን እንፈጥራለን- የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራቂ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ስም በዓለም ከፍ አድርገው የሚያስጠሩ ቴክኖሎጂዎችን እንፈጥራለን- የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራቂ ተማሪዎች
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አደራ በመቀበል የሀገራቸውን ስም የሚያስጠሩ ችግር ፈች ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር እንደሚተጉ የ2016 ሰመር ካምፕ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ላለፉት ሁለት ወራት ሲያሰለጥናቸው የነበሩ የ2016 ሰመር ካምፕ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
በስልጠናው ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 200 ተማሪዎች ስለ ኮምፒውተር ቋንቋ፣ ስለ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ ትንተና፣ ስለ ማሽን ማላመድና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ጉዳዮች በቂ ስልጠና መከታተላቸው ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምርቃቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተማሪዎች ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያራምድ ራዕያቸውን ለማሳካት እንዲተጉ አደራ ብለዋል።
ያነጋገርናቸው ሰልጣኞች በበኩላቸው ስልጠናው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ በቂ እውቀት ያገኙበት፣ በተግባር የታገዘና ለፈጠራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
የ11ኛ ክፍል ተማሪው ኖላዊ ሰይፈ ፥ በስልጠናው ያገኙት እውቀት በተግባር ልምምድ የታገዘና ለፈጠራ መንገድ ከፋች ነበር ብሏል።
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ወስዶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ውጤት በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ተማሪ ናሆም መስፍን፥ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀት አስፈላጊ ስለሆነው የኮምፒውተር ቋንቋ ሌሎች መሰረታውያን ግንዛቤ ማግኘቱን ተናግሯል።
የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ መልካም አስራት በበኩሏ፥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ ፕሮጀክትን እውን የማድረግ የሀሳብ አድማሷን ወደ ተግባር የሚለውጥ ስልጠና ማግኘቷን አንስታለች።
ተማሪ ኮኬት ግርማ ስልጠናው ውስን ግንዛቤ በነበራት ጉዳዮች ላይ በቂ እውቀት የጨበጠችበትና አርቲፊሻለ ኢንተለጀንስን የተረዳችበት ስልጠና መሆኑን ተናግራለች።
ተማሪዎቹ ሀገራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ፕሮጀክቶችንም ፈጥረዋል።
ለአብነትም ተማሪ ኖላዊ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ "የማዳበሪያ አጠቃቀም አማካሪ" መተግበሪያን መስራቱን ያነሳል።
በዚህም በሀገሪቱ ያለውን የማዳበሪያ አጠቃቀም ችግር በመቅረፍ የአፈርን መጎዳት ለመከላከል ግብ ይዟል።
መተግበሪያው የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮቹ በቀላሉ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀምን ለማስረዳት ያግዛቸዋል ነው ያለው።
ተማሪ መልካም በበኩሏ የኮሌራ በሽታ አምጭ ተህዋስን በውሃ ውስጥ መኖር አለመኖሩን የሚለይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያ መፍጠሯን ገልጻለች።
መሳሪያው ወደ ተግባር ቢውል ለሀገሯና ለአፍሪካ የኮሌራ ችግርን ለመቅረፍ ያስችላል ትላለች።
የዲጅታል መሳሪያዎችን የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲኖራቸው የማላመድና መረጃን ተንትኖ ውሳኔ የመስጠት ፕሮጀክትን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ የተናገረው ደግሞ ተማሪ ናሆም ነው።
አሁን ላይ በሀገሪቱ የዳታ ማዕከል እየተስፋፋ መምጣቱና ዲጅታል የመረጃ ማሰባሰብ ስራዎች መጀመራቸውም ለእርሱና መሰል ፕሮጀክቶች መሳካት እንደሚያግዝ ነው ያነሳው።
ተማሪዎቹ አክለውም አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የዲጅታላይዜሸን ስራዎችና መሰረተ ልማቶች ለፈጠራ ስራዎቻቸው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሰጣቸው አደራ ለለውጥ የሚያነሳሳ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሀገራቸውን በእውቀትና በትጋት በማገልገልና ችግር ፈች ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጣቸውን አደራ እውን እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
በቴክኖሎጂው መስክ ኢትዮጵያን የሚያኮራ እና ስሟን በዓለም ከፍ አድርጎ የሚያስጠራ ፈጠራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።