የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 36 ሺህ 409 ፈተናውን አልፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 36 ሺህ 409 ፈተናውን አልፈዋል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 36 ሺህ 409 ፈተናውን ማለፋቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 674 ሺህ 823 ተማሪዎች መካከል 36 ሺህ 409 ተማሪዎች ፈተናውን ማለፋቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች 5 ነጥብ 4 በመቶ አልፈዋል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
የዘንድሮው ዓመት አጠቃላይ ውጤት ካለፉት ሁለት ዓመታት አንጻር የተሻለ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል ከ600 ከታረመው ፈተና ከፍተኛው ውጤት 575 መሆኑን ተናግረዋል።
ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 1 ሺህ 220 የሚሆኑት ከ500 በላይ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል።
ከነዚህም መካከል 384 ቱ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤታቸውን ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ማየት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡