በጎንደር እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማውን ታሪካዊነትና የቱሪስት መዳረሻነት በሚያጎላ መንገድ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማውን ታሪካዊነትና የቱሪስት መዳረሻነት በሚያጎላ መንገድ እየተከናወነ ነው

ጎንደር ፤ ጳጉሜን 4/2016 (ኢዜአ)፡- በጎንደር እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማውን ታሪካዊነትና የቱሪስት መዳረሻነት በሚያጎላ መንገድ በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በፌደራል መንግስት ድጋፍ በጎንደር ከተማ እየተካሄዱ የሚገኙ የፒያሳ የኮሪደር ልማትና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ዓለም አቀፍ ቅርስ የጥገና ስራ ጎብኝተዋል፡፡
በዚህ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ በጎንደር ከተማ በሀገራችን ከሚገኙ ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ልምድና ተሞክሮ በማስፋት በጎንደር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከጠበቁት በላይ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘርፉን ባለሙያዎችን በመመደብ የጎንደር የኮሪደር ልማት የከተማውን ታሪካዊነት በጠበቀ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጎንደር ፒያሳ የሚገኙ ህንጻዎች ታሪካዊ አውዳቸውንና ገጽታቸውን በጠበቀ መንገድ እየተካሄደ ያለው የእድሳት ስራ የከተማውን የቱሪስት መዳረሻነት በማጉላት የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ጎንደር ከተማ ካሏት በርካታ ቅርሶች አንጻር የኮሪደር ልማቱ ትርጉም ባለው መንገድ የቅርሶችን ታሪካዊ ፋይዳ ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ እየተካሄደ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲውል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠው፤ የነበራቸው ቆይታም የተሳካ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
''በፌደራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት አዲስ የስራ ባህል የፈጠረ ነው'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
የኮሪደር ልማቱ ምሽት ጭምር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ የከተማው ማህበረሰብም ልማቱን በመደገፍ እያደረገ ያለው ትብብርና ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ለቀጣይ የልማት ስራዎች ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ ከመሆኑም በላይ በርካታ የልማት ስራዎችን ማከናወን እንደሚቻል ተሞክሮ፣ ልምድና አቅም የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነው የከተማው የኮሪደር ልማት ፒያሳን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ቅርስ በሆነው በአጼ ፋሲል አብያተ መንግሰት ዙሪያ የሚከናወን መሆን ጠቁመው፤ ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም በራሱ በጀት በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች የኮሪደር ልማቱን ለማስፋት የሚያስችል አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጥናትና ዲዛይን ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጎንደር ከተማ ጋር የእህትማማች ከተሞች ግንኙነት ከመሰረተ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርብ የኮሪደር ልማቱን ለማሳካት እያደረጉት ላለው ድጋፍ በከተማ መስተዳድሩና በህዝቡ ስም ምሰጋና አቅርበዋል፡፡
በጉብኝቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰውና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ ሌሎችም የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት ተገኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት ፤ከተሞቻችንን ለወደፊቱ ለዜጎቻችን ክብር የሞላበት የኑሮ ዘይቤን ለማጎናፀፍ የሚመቹ እንዲሆኑ ማዘጋጀት ይኖርብናል፤ ከተሜነት እየተስፋፈ የሚሄድ መሆኑ የታወቀ ነው፤ እኛም ዘላቂ እና ምቹ ከተሞችን ለመፍጠር ሁሉም መሳሪያዎች አሉን ማለታቸው ይታወሳል።
ከመጀመሪያው የሥራ ምዕራፍ ብዙ ትምህርቶች ቀስመናል፤ አሁን ለሚቀጥለው ምዕራፍ ባላሰለሰ የመሻሻል ሂደት እና የሥራ ሥነምግባር በቀደመው ያሳካነውን ለማላቅ ተነስተናል ብለዋል።
ዛሬ የአዲሶቹን ኮሪደሮች ልማት በይፋ ስናስጀምር ልማቶቹ እና ጥገናዎቹ ከደረስንበት ምዕራፍ አልፈው የሚሻገሩ መሆናቸውን ማስታወስ ይገባናል ሲሉ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ይህን ጠቃሚ ሥራ ለማስፋፋት በምናደርገው ጥረት የተሰሩት ኮሪደሮች የሥራ መሪዎች በመላው ሀገራችን ተመሳሳይ ሥራ ለጀመሩ አስራ አንድ ከንቲባዎች ረዳት በመሆን ያገለግላሉ ሲሉ በወቅቱ ገልጸዋል።