ቀጥታ፡

የላባችን ውጤት የሆነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መገባደድ ደረጃ ላይ ማድረስ የቻልነው ሀገራዊ አቅማችንን ደምረን በሕብር ስለሰራን ነው - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ የላባችን ውጤት የሆነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መገባደድ ደረጃ ላይ ማድረስ የቻልነው ሀገራዊ አቅማችንን ደምረን በሕብር ስለሰራን ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ከ150 በላይ ለሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በመርኃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፓርቲያችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘገብናቸው ድሎች የሕብር ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ህብር ለኢትዮጵያ እውነትም መልክም ነው ያሉት አቶ አደም በሀገራችን የአስተሳሰብ፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሀይማኖት ብዙሃነት መልኮቿ፣ ገጾቿ፣ ውበቷ፣ በረከቶቿ በአግባቡ ማስተናገድ ለሕብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


 

ትላንት ነጻነታችንን በደማችንና በአጥንታችን ማስከበር የቻልነው ሕብራዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደምሮ በአንድነት በሕብር በመቆሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመን የሀገራችንን ህልውና ማስጠበቅ የቻልነው በሕብር ነው ማለታቸውን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የላባችን ውጤት የሆነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መገባደድ ደረጃ ላይ ማድረስ የቻልነው ሀገራዊ አቅማችን ደምረን በሕብር ስለሰራን ነውም ብለዋል አቶ አደም በመልዕክታቸው፡፡

እኛ ኢትዮጰያውያን በሕብርና በጋራ እንዴት እንደቆምን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲገጥሙን የምንሻገረው በሕብር መሆኑን ጠቁመው በጎፋ ዞን የተከተሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ የተንጠባረቀውን ርብርብ በማሳያነት አንስተዋል፡፡


 

ቀጣይ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ጠንካራና ሉዓላዊነቷና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው በህብር ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ በህብር የተፈጠረ፣ በሕብር የሚያምን እንደዚሁም ሕብርን ለማጽናት የሚታገልና የራሱን ህብር የሚጸና ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡

አጠቃላይ ሀሳቦቻችን፣ ራዕያችን፣ መርሆቻችን፣ አደረጃጀቶቻችን፣ አሰራሮቻችንና ስኬቶቻችን ይህንን ያረጋግጣሉ ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም