የዌብ ወንዝ ድልድይ ዳግም ተጠግኖ ለህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ክፍት ሆነ -- የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የዌብ ወንዝ ድልድይ ዳግም ተጠግኖ ለህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ክፍት ሆነ -- የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
ሮቤ ጳጉሜን 04/2016 (ኢዜአ)፤ የዌብ ወንዝ ድልድይ ዳግም ተጠግኖ በጊዜያዊነት ለህዝብ ማመላለሻ ክፍት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የሮቤ-አሊ-ጋሠራ-ጊኒር መንገድ ላይ የሚገኝ የብረት ድልድይ በደረሰበት ጉዳት በመንገዱ የሚደረግ ጉዞ መቋረጡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ድልድዩ በመሰበሩ ምክንያት መንገዱ ለጥቂት ቀናት ለትራፊክ ዝግ እንደሚሆን መግለጹ ይታወሳል።
በወቅቱ 450 ኩንታል ስንዴ ጭኖ በድልድዩ ላይ ለማለፍ የሞከረ ተሽከርካሪ ተገጣጣሚ ብረት ድልድዩን በመደርመሱ መንገዱ መዘጋቱን የመንገዶች አስተዳደሩ ገልጾ ነበር።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የባሌ አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አመንሲሳ ታደሰ፣ ድልድዩን ጠግኖ ዳግም ለአገልግሎት ለማብቃት በአካባቢው የሚገኙ የመንገድ ተቋራጮችን በማሳተፍ ዳግም ለትራፊክ ክፍት ማድረግ ማቻሉን ገልጸዋል።
የተሰበረውን የብረት ድልድይ እና ከነጭነቱ የወደቀውን ተሳቢ የጭነት መኪና የማንሳትና አዲሱን ድልድይ በቦታው የመተካት ሥራ በጥንቃቄ መከናወኑን አመልክተዋል።
በአካባቢው ላይ የነበረው ዝናባማ የአየር ፀባይ ሥራውን በሚፈለገው ፍጥነት ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ ቢያደርገውም አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው ርብርብ በስኬት መጠናቁን ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብም ድልድዩ ተጠግኖ ዳግም ለአገልግሎት እንዲበቃ በትዕግስት በመጠበቁና ሥራውን መደገፍ ከአስተዳደሩ ጎን በመሆኑ አመስግነዋል።
ድልድዩ ከዛሬ ጀምሮ ለህዝብ ማመላለሻና አነስተኛ ክብደት ላለቸው ተሽከርካሪዎች ብቻ በጊዜያዊነት ክፍት መደረጉን ገልጸው፣ ከ40 ቶን በታች ለሚመዝኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሦስት ቀን በኋላ ክፍት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
''በድልድዩ ከ40 ቶን ክብደት በላይ የጫነ ተሽከርካሪ ማለፍ አይችልም፣ አሽከርካሪዎችም ለመንገዱ በተፈቀደው ክብደት አግባብ ብቻ መጠቀም አለባቸው'' ብለዋል።
ባሌ ዞን የሮቤ-አሊ-ጋሠራ-ጊኒር መንገድ ላይ የሚገኘው የዌብ ወንዝ የብረት ድልድይ ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በደረሰበት ጉዳት በመንገዱ የሚደረግ ጉዞ መቋረጡና ድልድዩን ለመጠገን ሲደረግ የነበረው ርብርብ ይታወሳል።