በክልሉ "የኅብር ቀን" የስፖርት ዘርፉን በማነቃቃት የእርስ በእርስ ግንኙነትን በሚያጠናክር አግባብ ታስቦ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ "የኅብር ቀን" የስፖርት ዘርፉን በማነቃቃት የእርስ በእርስ ግንኙነትን በሚያጠናክር አግባብ ታስቦ እየተከበረ ነው
ባህርዳር፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል "የኅብር ቀን"ን የስፖርት ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ ሰላምንና የእርስ በእርስ ግንኙነትን በሚያጠናክር አግባብ ታስቦ እየተከበረ መሆኑን የክልሉ ወጣትና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
ጳጉሜን 4 ''የኅብር ቀን'' የባህር ዳር ከተማ እና ሰሜን ጎጃም ዞን በጋራ በስፖርታዊ ጨዋታዎችና በሰብዓዊ ድጋፍ ታስቦ በመከበር ላይ ይገኛል።
የክልሉ ወጣትና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ እንዳሉት፤ ፤ ስፖርት ህብረ ብሄራዊነትን በመጠበቅ ለጋራ ግብ በጋራ መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው።
"የኅብር ቀን" በክልሉ የስፖርት ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ ሰላምንና የእርስ በእርስ ግንኙነትን የበለጠ በሚያጠናክር አግባብ ታስቦ በመከበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በክልሉ የስፖርት ዘርፉን በመደገፍ በአካል ብቃቱ የጎለበተ ትውልድ ከመገንባት ባሻገር ህብረ ብሔራዊነትን በማጉላት ለላቀ ስኬት የሚያበቁ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና የሰሜን ጎጃም ዞን በጋራ "የኅብር ቀን"ን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ መከበሩ ቀኑን የበለጠ እንዲጎላ እንዳደረገው አስረድተዋል።
ስፖርት አካላዊና አዕምሯዊ ብቃቱ የተሟላ ዜጋ ከማፍራት ባሻገር የአንድነትና የጥንካሬ መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ናቸው።
ስፖርት የሰላም መሆኑን ጠቅሰው፤ "የኅብር ቀን" ሲከበርም ሰላምንና አንድነትን ይበልጥ በሚያጎለብት አግባብ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
መረሃ-ግብሩ በስፖርታዊ ጨዋታና በሰብዓዊ ድጋፍ ታስቦ እየተከበረ ሲሆን፤ በአከባበሩ ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልል፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር፣ የሰሜን ጎጃም ዞን አመራር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ጳጉሜን -4" ኅብራችን ለሰላማችን" በሚል መሪ ሃሳብ " የኅብር ቀን" የኢትዮጵያዊያን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት፣ መልክዓ ምድርና ማኅበራዊ መስተጋብር በሚያንጸባርቅ መልኩ ታስቦ ይውላል።
የኢትዮጵያዊያን ኅብረ ብሔራዊ ማንነት የጥንካሪ መሰረት በመሆኑ በዕለቱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተንጸባርቆ እንደሚውልም ታውቋል።