ከምርምር ማዕከሉ ከተገኘው የበቆሎ ምርጥ ዘር የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ከምርምር ማዕከሉ ከተገኘው የበቆሎ ምርጥ ዘር የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - አርሶ አደሮች

ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 3/2016 (ኢዜአ):- ከባኮ ብሔራዊ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ካገኙት የበቆሎ ምርጥ ዘር የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የምርምር ማዕከሉ ከሀዋሳ የበቆሎ ምርምር ንዑስ ማዕከል ጋር በመተባበር የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በጋሎ ኡርጌሳ ቀበሌ አካሂደዋል።
በመስክ ቀኑ ላይ ከሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የተውጣጡ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች ፣ተመራማሪዎችና የዘር ብዜት ማዕከላት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የባኮ ብሔራዊ በቆሎ ምርምር ማዕከል ከሀዋሳ የበቆሎ ምርምር ንዑስ ማዕከል ጋር በመተባበር ሁለት የበቆሎ ዝርያ ምርጥ ዘሮችን በአርሶ አደሮች ኩታ ገጠም ማሳ ላይ የማላመድ ስራ እያከናወነ ነው።
በጋሎ ኡርጌሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሳሁን ሻምበል እንዳሉት ምርጥ ዘሩን እንዳገኙ እየጣለ ያለውን ዝናብና እርጥበት ተጠቅመው ዘርተዋል።
የበቆሎ ቡቃያው አሁን ላይ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አመልክተዋል።
ዝርያው ቀድሞ ሲያለሙት ከነበረው በቆሎ ዝርያ አንጻር ድርቅና፣ በሽታን መቋቋም የሚችል ከመሆኑ ባለፈ ጥሩ ምርት እንደሚሰጥ ለመረዳት መቻላቸውን ገልጸዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሌላው አርሶ አደር አየለ ጉጉዶ በበኩላቸው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ስድስት ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ 'ቢኤች 520' በተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።
ከዘራን በኋላ በቡቃያ ደረጃ ባለበት ወቅት ዝናብ በመቋረጡ ሰብሉ ይጠፋል ብለን ሰግተን ነበር ያሉት አርሶ አደሩ ይሁን እንጂ በቆሎው የፀሐይ ሙቀት ተቋቁሞ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ከሚዘሩት በቆሎ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት ያገኙ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከ60 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ዝርያው በቶሎ በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል።
የባኮ ብሔራዊ በቆሎ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዋቁማ ቢራቱ እንዳሉት ማዕከሉ ከሀዋሳ የበቆሎ ምርምር ንዑስ ማዕከል ጋር በመተባበር በአካባቢው 'ቢኤች 520' እና 'ቢኤች 5211' የተሰኙ ሁለት አይነት ዝርያዎችን እያላመደ ይገኛል።
የበቆሎ ዝርያዎቹ ምርታማነትንና በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ እንዲሁም የተመጣጠነ የምግብ ንጥረ ነገር የያዙ ለአካል እድገትና መዳበር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
አርሶ አደሩ በሄክታር መጠቀም ያለበትን የአፈር ማዳበሪያ በተሟላ መንገድ ጥቅም ላይ ካዋለ በሄክታር እስከ 100 ኩንታል ምርት መስጠት የሚያስችሉ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በአርሶ አደሩ የመስክ ቀን ከተገኘው ግብረ መልስ በቆሎው ምርታማ፣ ድርቅና በሽታን የሚቋቋም ፈጥኖ የሚደረስ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለም ተናግረዋል።
በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል የበቆሎ ድቀላ ተመራማሪና የሀዋሳ የበቆሎ ምርምር ንዑስ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ይድነቃቸው መርዕድ እንዳሉት 'ቢኤች 5211' እና 'ቢኤች 520' ዝርያዎች ምርታማ የሆኑ አዲስ የምርምር ውጤቶች ናቸው።
የበቆሎ ዝርያዎቹ በአካባቢው ያለውን ዝናብ እጥረት በመቋቋም ከደረሰ በኋላም አረንጓዴ ሆኖ የሚቆይና በአንድ አገዳ ላይ እስከ ሁለት በቆሎ የሚይዝ በመሆኑ በአርሶ አደሩ ተፈላጊ እንድሚያደርገው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የሀዋሳ ምርጥ ዘር ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ አናጋው በአርሶ አደሮች የመስክ ቀን ላይ የቀረቡት ውጤታማ የሆኑ የበቆሎ ዝርያዎችን በቀጣይ አመት አባዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የአርሶ አደሩን የዘር ፍላጎት ለማሟላት በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በሌሎች ክልሎች ከ4 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ዘር እያባዛ መሆኑን ተናግረዋል ።
ከዘር ብዜቱም ከ90 ሺህ እስከ 100 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።