ቀጥታ፡

በክልሉ የህብር ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው

ሰቆጣ/ ደሴ፤ ጳጉሜን 4/2016 ዓ/ም (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የጳጉሜን 4 '' የህብር ቀን'' በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።  

የጳጉሜን 4  የህብር ቀን " ኅብራችን ለአንድነታችንና ለዘላቂ ሰላማችን'' በሚል መሪ ሀሳብ በደሴ እና በሰቆጣ ከተሞች በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ህብር የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ መገለጫ በመሆኑ ይህንኑ ጠብቀን ሰላማችንና ልማታችንን ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

ቀኑን ስናከብር በመረዳዳት፣ በመተጋገዝና በመተሳሰብ መሆን አለበት ያሉት ከንቲባው በህብር የከተማችንን ሰላም መጠበቅ መቻላችን ሰፋፊ የልማት ስራዎችን በማከናወን ለአገልግሎት እንዲበቁ አድርጓል ብለዋል።



የደሴ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው በበኩላቸው፤ ህብረ ብሄራዊነታችንን ጠብቀን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስራት ጤናችንንና ሰላማችንን ልንጠብቅ ይገባል ነው ያሉት።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር አይነተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የተለያዩ የአመራር አባላት የተገኙ ሲሆን በአካል ብቃት እንቅስቃሴና ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ተከብሯል።

በተመሳሳይም በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ የጳጉሜን 4 የህብር ቀን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተከብሯል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፓርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱራህማን መኮንን እንዳሉት ብቁና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።


 

የአስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ በበኩላቸው የፀጥታ መዋቅሩ የህብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ የህዝብን ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሃይሎችን ለመመከት ቀዳሚ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል። 

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት አቶ ዘሩ የማነብርሃን እንዳሉት፤ ህብረ ብሔራዊ መገለጫዎቻችን የአንድነታችን መሰረት ናቸው። 

ስፓርት የአንድነትና የፍቅር መገለጫ መሆኑን ገልፀው፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቋሚነት መከናወን እንዳለበት አመልክተዋል። 

''አንድነትና ህብረ ብሔራዊነትን ለማጠናከር ስፓርት ትልቅ መድረክ ነው'' ያሉት ደግሞ አቶ ሚካኤል ሲሳይ ናቸው። 

ብቁና ጤናማ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ስፓርት ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም