ቀጥታ፡

ህብረትና አንድነትን በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ

ሶዶ፣ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ህብረትና አንድነትን በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ።

የህብር ቀን "ኅብራችን  ለአንድነታችንና ለዘላቂ ልማታችን" በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ በማስ ስፖርት፣ አካላዊ እንቅስቃሴና በሌሎች መርሃ-ግብሮች እየተከበረ ነው። 

በወቅቱም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ዮሐንስ በየነ ባስተላለፉት መልዕክት የቆየ ህብረታችንንና አንድነታችንን በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የጀመርነውን ጥረት በላቀ ትጋት እናስቀጥላለን ብለዋል።

ብዝሃ ቋንቋችንንና ባህላችንን እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደን የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር ሁለንተናዊ ብልፅግናን ልናረጋግጥ ይገባል ብለዋል።


 

"ብዝሃነታችን ስጋት ሳይሆን በአብሮነትና በመዋደድ እሴቶች ለሰላምና ልማታችን ምሰሶ ሆኖ ሲያገለግለን ቆይቷል" ሲሉም ተናግረዋል።

አምስቱን የጳጉሜ ቀናት በተለያዩ ሁነቶች አስበን ማክበራችን ያለፈው ዓመት ድክመቶቻችንን በማረም በአዲሱ ዓመት በአዲስ መነሳሳት የጋራ ጥረትን ለማጠናከር እንዲቻል ነው ሲሉም አክለዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ወልደማሪያም በበኩላቸው ህብረትና አንድነት ለጋራ ስራ ስኬት መሠረት መሆኑን ገልፀዋል።

''የኢትዮጵያ ቀደምት የጀግንነት ታሪኮች በአንድነትና በህብረት የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸው እኛም በተሰጠን በዚህ ዘመን ሰርተን የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ ይገባናል'' ብለዋል።


 

በመሆኑም ሁሉም ህብራዊነቱን በማጠናከር በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን ሊጥር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ንጉሴ መንግስቱ በሰጡት አስተያየት "የቋንቋችን፣ የባህላችን እንዲሁም የእምነታችን ልዩነቶች ከውበት አልፈው የአንድነታችንና የአብሮነታችን ተምሳሌት ናቸው" ብለዋል።

የህብር ቀን በአካል ብቃት እንቅስቃሴና በማስ ስፖርት መወሳቱ አብሮነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ለልማት ተያይዘን ለመነሳሳት በተለይም በአዲስ ዓመት አዲስ ራዕይና ግብ ይዘን እንድንሰራ ያግዛል ብለዋል።

''የሀይማኖትና የዘር ልዩነት ሳይፈትነን ለበርካታ ዓመታት በዕድር በማህበሩ በጋራ ስንሰራና ስንጠቀም ኖረናል'' ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሪት ወርቄ ለማ ናት።

አሁንም ልዩነታችን ለአንድነታችን አቅም እንደሚሆን በመገንዘብ ለጋራ ተጠቃሚነታችን እንሰራለን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም