ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ታደርጋለች
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ የሜዳ ጨዋታውን ዛሬ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያካሂዳል።
የብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰዓት 60 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ይከናወናል።
በምድብ 8 የምትገኘው ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከታንዛንያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየቷ ይታወቃል።
ውጤቱንም ተከትሎ በአንድ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ተጋጣሚው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው የጊኒ አቻውን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።
በ48 ዓመቱ ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ሰባስቲየን ዲሳብሬ የሚመራው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን በሶስት ነጥብ ምድቡን እየመራ ይገኛል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ ባሉት ቀናት ልምምዱን በታንዛንያ ሲያደርግ ቆይቷል።
ዋልያዎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት ማምሻውን ጨዋታው በሚካሄድበት ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ማድረጋቸውን ኢዜአ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በልምምድ ላይ ህመም አጋጥሞት የነበረው አብነት ደምሴ እንዲሁም ጉዳት ላይ የነበረው ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ልምምድ መመለሳቸውንም ገልጿል።
ሀገራቱ በሁሉም ውድድሮች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 6 ጨዋታዎች ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አራት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ አሸንፋ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ 143ኛ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 6ዐኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የ38 ዓመቱ አልጄሪያዊ ላህሉ ቤንብራሃም የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።
በምድብ 8 የሚገኙት ጊኒና ታንዛንያ ነገ ከምሽቱ 1 ሰዓት ኮትዲቯር በሚገኘው ቻርልስ ኮናን ባኒ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 48 ሀገራት በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።