የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመዝጊያ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመዝጊያ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2016 (ኢዜአ)፦ የ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመዝጊያ ስነ ስርዓት 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ከነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በፓሪስ የተካሄደው ውድድር ዛሬ ተፈጽሟል።
በውድድሩ ላይ ከ168 አገራት የተወጣጡ ከ4000 በላይ አትሌቶች በ22 የስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል።
በተጨማሪም የፓራሊምፒክ የስደተኞች ቡድንና በዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የተወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችም ተሳታፊ ሆነዋል።
ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች ተወዳድራለች።
ኢትዮጵያ በ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ 2 የወርቅና 1 የብር በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 44ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ በዘንድሮው ፓራሊምፒክ ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት እ.አ.አ በ2021 በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ካገኘችው አንድ የወርቅ ሜዳሊያ የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ቶኪዮ ላይ 56ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በፓሪስ በ1500 ሜትር ሴቶች የጭላንጭል(T-13) ፍጻሜ ለኢትዮጵያ በውድድሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቷ ይታወቃል።
አትሌት ያየሽ ጌቴ በ1500 ሜትር ሴቶች ሙሉ በሙሉ የአይነ ስውር(T-11) ውድድር በ 4 ደቂቃ ከ27 ሴኮንድ ከ68 ማይክሮ ሴኮንድ በራሷ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን በአራት ሴኮንድ በማሻሻል አሸናፊ ሆናለች።
አትሌት ይታያል ስለሺ በ1 ሺህ 500 ወንዶች አይነ ስውር ጭላንጭል (T-11) ፍጻሜ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በ1500 ሜትር የእጅ ጉዳት (T-46 ምድብ) ወንዶች ፍጻሜ የተወዳደረው አትሌት ገመቹ አመኑ ስምንተኛ መውጣቱ ይታወቃል።
ቻይና፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ አሜሪካ፣ ኔዘርላንድና ብራዚል በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃን በመያዝ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ በቀዳሚነት ስፍራ ላይ ተቀምጠዋል። አዘጋጇ ፈረንሳይ ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በውድድሩ 84 አገራት ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል።
ከአገራት በተጨማሪ የፓራሊምፒክ የስደተኞች ቡድንና በዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የተወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶች ሜዳሊያ አግኝተዋል።
በአሁኑ ሰዓት የ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመዝጊያ ስነ ስርዓት ማምሻውን 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም እየተካሄደ ይገኛል።
በስነ ስርዓቱ ላይ ሙዚቀኞችን ጨምሮ 28 የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስራቸውን ያቀርባሉ።
አካል ጉዳተኛዋ አሜሪካዊ ሙዚቀኛ፣ የቫዮሊን ተጫዋች፣ፀሐፊና ተሟጋች ጋሊን ሊ፣ አሜሪካዊው አካል ጉዳተኛ የሙዚቃ ባለሙያና የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ጋርኔት ሲልቨር-ሆል፣ አይነ ስውሩ አሜሪካዊ የጃዝ ፒያኖ ተጫዋች ማቲው ዊቴከርና አሜሪካዊው ሙዚቀኛና ራፐር አንደርሰን ፓክ ስራዎችቻቸውን ከሚያቀርቡ ባለሙያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የ18ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጇ ሎስ አንጀለስ ከተማ የፓራሊምፒክ ባንዲራን ከፓሪስ ትረክባለች።
See insights and ads
All reactions:
1212