ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀው ''ጉዞ ወደ አገር ቤት'' የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል ዛሬ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀው ''ጉዞ ወደ አገር ቤት'' የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል ዛሬ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2016(ኢዜአ)፦ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀው ''ጉዞ ወደ አገር ቤት'' የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል በአድዋ ድል መታሰቢያ ዛሬ መጀመሩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።
ፌስቲቫል ከዛሬ ጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በፌስቲቫሉ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የኪነ ጥበብ ትሪኢቶችና ሌሎች መርኃ ግብሮችተካተዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ፌስቲቫሉን በስኬት ለማከናወን የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
ይህንንም ተከትሎ ፌስቲቫሉ ዛሬ መጀመሩን ጠቅሰው በፌስቲቫሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ወደአገራቸው የገቡ ወጣቶች በዋነኝነት እየተሳተፉ መሆኑ ገልጸዋል።
ፌስቲቫሉም የእውቀት፣ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር በዘርፈ ብዙ መንገድ የተጠናከረ የሥነ-ልቦና ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።