17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2016 (ኢዜአ)፦ በፓሪስ እየተካሄደ የሚገኘው 17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።
ከነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ እየተካሄደ ባለው ውድድር ከ168 አገራት የተወጣጡ ከ4000 በላይ አትሌቶች በ22 የስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል።
በተጨማሪም የፓራሊምፒክ የስደተኞች ቡድንና በዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የተወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችም ተሳታፊ ሆነዋል።
ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች ተወዳድራለች።
ኢትዮጵያ በ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ 2 የወርቅና 1 የብር በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ በዘንድሮው ፓራሊምፒክ ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት እ.አ.አ በ2021 በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ካገኘችው አንድ የወርቅ ሜዳሊያ የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በ1500 ሜትር ሴቶች የጭላንጭል(T-13) ፍጻሜ ለኢትዮጵያ በውድድሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቷ ይታወቃል።
አትሌት ያየሽ ጌቴ በ1500 ሜትር ሴቶች ሙሉ በሙሉ የአይነ ስውር(T-11) ውድድር በ 4 ደቂቃ ከ27 ሴኮንድ ከ68 ማይክሮ ሴኮንድ በራሷ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን በአራት ሴኮንድ በማሻሻል አሸናፊ ሆናለች።
አትሌት ይታያል ስለሺ በ1 ሺህ 500 ወንዶች አይነ ስውር ጭላንጭል (T-11) ፍጻሜ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በ1500 ሜትር የእጅ ጉዳት (T-46 ምድብ) ወንዶች ፍጻሜ የተወዳደረው አትሌት ገመቹ አመኑ ስምንተኛ መውጣቱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በሁለት የወርቅና 1 የብር በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 43ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ቻይና፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ አሜሪካ፣ ኔዘርላንድና ጣልያን በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። አዘጋጇ ፈረንሳይ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመዝጊያ ስነ ስርዓት ዛሬ ማምሻውን 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ30 ጀምሮ ይካሄዳል።
በስነ ስርዓቱ ላይ ሙዚቀኞችን ጨምሮ 28 የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስራቸውን ያቀርባሉ።
አካል ጉዳተኛዋ አሜሪካዊ ሙዚቀኛ፣ የቫዮሊን ተጫዋች፣ፀሐፊና ተሟጋች ጋሊን ሊ፣ አሜሪካዊው አካል ጉዳተኛ የሙዚቃ ባለሙያና የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ጋርኔት ሲልቨር-ሆል፣ አይነ ስውሩ አሜሪካዊ የጃዝ ፒያኖ ተጫዋች ማቲው ዊቴከርና አሜሪካዊው ሙዚቀኛና ራፐር አንደርሰን ፓክ ስራዎችቻቸውን ከሚያቀርቡ ባለሙያዎች መካከል እንደሚጠቀሱ የአሜሪካው ኤንቢሲ ቴሌቪዥን ዘገባ ያመለክታል።
የ18ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጇ ሎስ አንጀለስ ከተማ የፓራሊምፒክ ባንዲራን ከፓሪስ ትረከባለች።