ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ አባቶቻችን የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት እንዳወረሱን ሁሉ ገድላቸውን በማስታወስ ልናከብረው ይገባናል - አቶ ሙስጠፌ ሙሐሙድ

ጅግጅጋ፤ ጳጉሜ 3/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ አባቶቻችን የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት እንዳወረሱን ሁሉ ገድላቸውን በማስታወስ ልናከብረው ይገባናል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ተናገሩ።

"ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ የሉዓላዊነት ቀን" በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተከብሮ ውሏል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድን ጨምሮ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

በክብረ በዓሉም በለውጥ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተገዳደሩ ፈተናዎችን በመቋቋም የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማፅናት የተሰሩ ሥራዎች በፊልም ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ባስተላለፉት መልዕክት "አባቶቻችን አንድነቷና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር እንዳወረሱን ሁሉ ገድላቸውን በማስታወስ ልናከብረው ይገባናል" ብለዋል።


 

ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ የአባቶቻችንን አደራ የአሁኑ ትውልድ ሊያስቀጥል እንደሚገባ ገልጸው፤ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረትና በሁሉም መስክ ትጋታችንን በማጠናከር የተሟላ ነፃናትና ሉዓላዊነት ማምጣት ይጠይቃል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በርዕሰ መስተዳድሩ የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ተዘምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በታማኝነት ግብራቸውን ሲከፍሉ የቆዩ ግብር ከፋዮችም የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም