በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሉዓላዊነት ቀን ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሉዓላዊነት ቀን ተከበረ
አሶሳ፤ጳጉሜ 3/2016 (ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሉዓላዊነት ቀን ''ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት'' በሚል መሪ ሐሳብ በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ተከብሯል።
በአከባበር ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ባስተላለፉት መልዕክት "የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የተዋደቁ ጀግኖች የከፈሉትን ዋጋ በክብር ማሰብና ማመስገን ይገባል" ብለዋል።
አቶ አሻድሊ ይህን የሉዓላዊነት ቀን በመገባደድ ላይ በሚገኘው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ቦታ ማክበራችን ልዩ ያደርገዋልም ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ ሁላችንም በጋራ መቆም አለብን" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብም በአገር ሉዓላዊነት ማስከበርና በልማቱ ያለበትን ሃላፊነት እንደ ትናንት መወጣት እንደሚገባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ የፀጥታ አካላት እና የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በተመሳሳይ ቀኑ በአሶሳ ከተማ በወታደራዊ ትርዒት፣ በእግር ጉዞ እና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በዕለቱም "የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በልጆቿ ይከበራል!" እና "በጋራ የሀገር ዘብ እንሆናለን!" የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።