ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር አንደራደርም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2016(ኢዜአ)፦ ሊነኩን የመጡ ከሩቅም ከቅርብም አሳፍረን መመለስ መለያችን ነው፤ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር አንደራደርም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ጳጉሜን 3/2016 "ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ በተከበረው የሉዓላዊነት ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ መርኃ ግብር ላይ ነው።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው፤ ኢትዮጵያ የሚለው ሥም ከነጻነት፣ ከክብር እና ልቆ ከመታየት ጋር በቀጥታ የተያያዝ መሆኑን አንስተዋል።

ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ኢትዮጵያ አንድም አገር ላይ ወረራ ፈጽማ አታቅም ብለዋል።

በአንጻሩ፤ በታሪካችን ሙሉ ግን ሊነኩን የመጡ ከሩቅም ከቅርብም አሳፍረን መመለስ ደግሞ ተግባራችን ማንነታችንና መለያችን ነው ሲሉ ገልጸዋል። 


 

አንነካም! ከመጡብን ግን አሳፍረን እንመልሳለን፤ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ማንንም አንደራደርም ብለዋል። 

ወደውጭ የምንሄደው ወድሞቻችን የእኛን የሙያ ድጋፍ ሲፈልጉ መሆኑን ገልጸው፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክፍላተ ዓለማት ለሰው ልጅ ሰላምና አብሮነት መስዋዕትነት መክፈል ልማዳችን ነውም  ብለዋል።   

ይህን ልምድ መከላከያ ሰራዊትም ሆነ አባላቱ ጠንቅቃችሁ የምታውቁት ብቻ ሳይሆን በተግባር የምትኖሩት የሕይወት ገጻችሁ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከየትኛውም የጎረቤት አገራት ጋር ምንም አይነት ግጭት ውስጥ አለመግባቷን ጠቅሰው፤ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የጎረቤት አገራት ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የልማት ውጥን መሳካት የራሱ አበርክቶ ስላለው መሆኑን አስረድተዋል። 

ነገር ግን በቅርብም በሩቅም ያሉ አካላት እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን፤ የሰው አንፈልግም፤ የሚፈልገንና የሚነካንን ግን እንደ ልማዳችን አሳፍረን እንመልሳለን ሲሉም አሳስበዋል።  


 

ኢትዮጵያ ከየትኛውም አገር ጋር ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ፍላጎት ይልቁንም ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ መሆኑን አስምረውበታል።   

የመከላከያ ሰራዊት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው በሚጠቅም መልኩ የተገነባ ሰራዊት መሆኑን አንስተው ይህ ሰራዊት ሰላም የሚያስጠብቅ ብቻ ሳይሆን ልማትን የሚያፋጥን ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል። 

በየትኛውም ሙያ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ሥራቸውን በትጋት በመከወን ለአገሪቱ ብልጽግና የበኩላቸውን እንዲያበረክቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም