ሉዓላዊነት በደምና በላብ የሚጠበቅ እሴት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ሉዓላዊነት በደምና በላብ የሚጠበቅ እሴት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 3/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደም ማጽናት የተቻለውን ያክል በኢኮኖሚው መስክ የተሟላ ሉዓላዊነት ለመጎናጸፍ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በሉዓላዊነት የተሰየመችው ጳጉሜ-3 ከማለዳው ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር የተከፈለን ዋጋ ክብር በመስጠት በተለያየ ዝግጅት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በድምቀት ተከብሯል።
በዚሁ ጊዜ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የሉዓላዊነት ቀን ለነፃነታችን ለማንደራደር ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ዕለቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ሉዓላዊነት በደምም በላብም የሚጠበቅ እሴት ነው ያሉት አቶ ተመስገን፥ አንድ አገር በደምም በላብም የሚጸና ሉዓላዊነት ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደም ማጽናት የተቻለውን ያክል በኢኮኖሚው መስክ የተሟላ ሉዓላዊነትን ማጎናጸፍ የሚያስፈልግ ብሔራዊ አርበኝነትን ተላብሶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፥ ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየ የማይደፈር ነፃነትን የተጎናጸፈች አገር መሆኗ የጥቁር ህዝቦች የሉዓላዊነት መገለጫ ተደርጋ ትወሰዳለች ብለዋል።
ቀደምት ኢትዮጵያዊያን በዓድዋ ተራሮች ያስመዘገቡት አንጸባራቂ የድል ታሪክም የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑ ትውልድም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
በመርኃ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮች፣የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዝግጅቱም ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዋጋ ለከፈሉ ክብር የመስጠት ሥነ-ሥርዓት በማካሄድ ዝግጅቱ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።