አዲስ አበባ አዲስ የሆነችባቸው ቀድሞ የሚያውቋት የውጭ ሀገር ዜጎች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ አዲስ የሆነችባቸው ቀድሞ የሚያውቋት የውጭ ሀገር ዜጎች
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 3/2016(ኢዜአ)፦"የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ሁነኛ ወዳጅ ነኝ" ይላሉ፤ በዲፕሎማሲው የካበተ ልምድ ያላቸው የቀድሞ የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ዴቪድ ፍራንሲስ።
ለሁለት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያን በቅጡ የሚያቋት የዓለም የጥቁር ሕዝቦች ማዕከል ቦርድ የወቅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዴቪድ ከመንፈቅ ዓመት በፊት አዲስ አበባን ጎብኝተው ነበር።
ከሰሞኑ ወደ አዲስ አበባ በድጋሚ ሲመጡ ግን "የማይታመን አስደናቂ ትዕይንት ገጠመኝ፤ አዲስ አበባን በሌሊት ስቃኛት ሻንጋይ ከተማ ያለሁ መሰለኝ" ይላሉ።
"የአዲስ አበባ ክትመት ለውጥ የማይታመን ነው" የሚሉት ፕሮፌሰር ዴቪድ፤ አዲስ አበባን በርግጥም የአፍሪካዊያን መኩሪያ ከተማችን ብለዋታል።
ከሰሞኑ የአፍሪካ ከተሞች ፎረምን ያስተናገደችው አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ ያሳየችው አዲስ ገጽታ፤ በክትመት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እንግዶችን ማስደመሟም አልቀረም።
አዲስ አበባን ቀደም ብለው የሚያውቋት በቻይናው ሳውዝኢስት ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ ፕሮፌሰሩ ዋንግ ዢንግፒንግ፤ ከፈረንጆቹ አቆጣጠር 2016 ወዲህ አዲስ አበባ ሲመለሱ ከተማዋ አዲስ ሆናባቸዋለች።
መሰረተ ልማቷ፣ ፓርኮቿ እና ኪነ ህንጻዎቿ አስደናቂ እምርታ የታየባቸው መሆኑን ፕሮፌሰር ዋንግ ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የታየው የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ ቀድሞ ለሚያውቋት የውጭ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለአዳዲስ እንግዶቿም ግርምት መፍጠሩ አልቀረም።
በፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ትብብር ተቋም የሰሃራ በታች የክትመት ጉዳዮች ተመራማሪዋ ሲና ሽልመር(ዶ/ር)፤ አዲስ አበባን ሲረግጡ የመጀመሪያቸው ቢሆንም ከተማዋን ያገኟት ከገመቱት በላይ ነው።
የአዲስ አበባ የከተማ ልማት ሂደት እንዳስደነቃቸው የሚናገሩት ተመራማሪዋ፤ የከተሞች ዘላቂ ዕድገት የሚረጋገጠው በጊዜ ሂደት መሆኑን የሀገራቸውን መዲና ፓሪስን ለአብነት በማንሳት ይጠቅሳሉ።
አዲስ አበባም አሁን በጀመረችው መልኩ ከቀጠለች በአጭር ጊዜ መሆን ወደምትፈልግበት ደረጃ እንደምትደርስ ነው የተናገሩት።