ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መረጋጋት በዋጋ የማይተመን መስዋዕትነት ከፍላለች− የሶማሌ ክልል አገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መረጋጋት በዋጋ የማይተመን መስዋዕትነት ከፍላለች− የሶማሌ ክልል አገር ሽማግሌዎች
ጅግጅጋ፤ ጳጉሜን 3/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በሶማሊያ ለዓመታት የቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም ልጆቿን ገብራ በዋጋ የማይተመን መስዋዕትነት በመክፈል ለአገሪቷ መንግስታዊ መረጋጋት ሚናዋን ስትወጣ መቆየቷን የሶማሌ ክልል አገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መንግስታት መካከል ያጋጠመ ችግርን ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር መፍታት እንደሚቻልም አመልክተዋል።
የሶማሌ ክልል የሰላምና አንድነት የአገር ሽማግሌዎች ሸንጎ የሥራ አስፈፃሚ አባል ሱልጣን አብዲ ፋራህ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ህዝቦች በብዙ መልኩ የተሳሰሩ ወንድማማቾች ናቸው።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ለዘመናት የቆየው የህዝብ ለህዝብ ትስስር ጠንካራ መሆኑን አውስተው፤ “ሶማሊያ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ መስዋዕት በመክፈል እንዲገታ ያደረገች፣ ዜጎቿ ሲሰደዱ ተቀብላ ያስተናገደችው ኢትዮጵያ ናት” በማለት የግንኙነታቸውን ጥልቀት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ህዝቦች ላይ በሽብር ቡድኖቹ ይደርስባቸው የነበረውን የግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመቀልበስ ከሰላም አስከባሪ ሀይል በፊት መግባቷን ያስታወሱት የሥራ አስፈፃሚ አባል ሱልማን አብዲ፤ በአገሪቷ አሁን ለሚታየው አንፃራዊ መረጋጋት መሰረት የጣለችው ኢትዮጵያ መሆኗን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በፍቅር የሚስተናገዱ የሶማሊያ ስደተኞች መኖራቸውን ገልጸው፤ እስከዛሬ ያለምንም ችግር በሰላም እየኖሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
በሶማሊያ የሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ሀይል የኢትዮጵያ የሰላም ስጋት ሊሆን እንደማይገባም አጽንኦት ሰጥተውታል።
"የኢትዮጵያና ሶማሊያ ህዝቦች ጠላት አይደሉም" ያሉት ሱልጣን አብዲ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ መንግስታት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ጉዳይ በውይይትና በሰላማዊ አካሄድ ብቻ መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የሶማሌ ክልል የሰላምና አንድነት የአገር ሽማግሌዎች ሸንጎ አባል ሱልጣን ሼኽ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለሶማሊያ ህዝብና መንግስት የማይረሱ ውለታዎች አበርክታለች።
የሶማሊያ የሽግግር መንግስት በአሸባሪዎች ምክንያት ወደ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ መግባት አቅቶት እንደነበር አስታውሰው፤ በወቅቱ ከባይደዋ ወደ ሞቃዲሾ በሚገኘው 'ቪላ ሶማሊያ' ቤተ መንግስት ያስገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ምክንያት “አሁን ያለው የሶማሊያ መንግስታዊ መዋቅርና ስርዓት በሁለቱ እግር እንዲቆም ያስቻለችው ኢትዮጵያ ናት ማለት እችላለሁ” ብለዋል።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መንግስት መካከል እየታየ ያለው ውጥረት ለሁለቱ አገሮች ጥቅም እንደሌለው የገለጹት ሱልጣን ሼህ ሀሰን፤ “የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ግብነት እድል ሳይሰጡ በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር መፍታት ይችላሉ” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
“በጎረቤት ሶማሊያ ለዓመታት የቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት ተከትሎ መንግሥታዊ መረጋጋት እንዲመጣ ኢትዮጵያዊያን እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል በዋጋ የማይተመን ሚና ተወጥተዋል” ያሉት ደግሞ የሶማሌ ክልል ሀገር ሽማግሌዎች ሸንጎ ዋና ፀሐፊ አቶ ሃሙድ ፊሌ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጦር የተሰማራበት አካባቢ ያለው ህዝብ ከአሸባሪዎች ከመታደግ ባለፈ ቅቡልነት ያለው መንግስት እንዲመሰረት የልማት፣ የሰላምና ዲሞክራሲ ሂደት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል ።
ዛሬ በአገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜን-3 “የሉዓላዊነት ቀን" በሚል ስያሜ “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ በመከበር ላይ ይገኛል።
All reactions:
99


