ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት ነው -ኢንጂነር አሸብር ባልቻ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት ነው -ኢንጂነር አሸብር ባልቻ
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 3/2016(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጎላ አበርክቶ ያለው ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጸ፡፡
ጳጉሜን 3 የሉዓላዊነት ቀን "ኅብር ለሁለንተናዊ ሉአላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ በመላ አገሪቱ በተለያዩ መርኃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዕለቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከጥንት እስከዛሬ ከክብር፣ ልቆ ከመገኘትና፣ ከነጻነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን የግዛት ሉአላዊነት ብቻውን እንደማይቆም በመጥቀስ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ነጻነትን በማረጋገጥ ሁለንተናዊ ሉአላዊነትን ዕውን ለማድረግ አዲስ አይነት ዐርበኝነት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያውያን ኅብር በጉልህ ከታየባቸውና የብሔራዊነት ዐርበኝነት ከተገለጠባቸው ተግባራት መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጫና የአንድነታቸው ካስማ ነው።
የግድቡ አራት ተርባይኖች ሀይል በማመንጨት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ፤ከእነዚህ ተርባይኖች መካከል ሁለቱ ሥራ የጀመሩት በተጠናቀቀው የነሀሴ ወር መሆኑን አስታውሰዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 13ቱም ተርባይኖች ወደ ሥራ ሲገቡ አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ባለፉት 70 ዓመታት ያመነጨችውን ጠቅላላ ሀይል በእጥፍ የሚያሳድግ ታሪክ ቀያሪ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም የህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጎላ አበርክቶ ያለው ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ሀይል ከማመንጨት ባለፈ ያመነጨውን ወደ ተጠቃሚዎች የማድረስ ሀላፊነቱን በትጋት እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ደግሞ ከህዳሴ ግድብ ባለፈ በኮይሻ፤ በጊቤ ሶስትና ሌሎች ማመንጫዎች በጥራትና በፍጥነት በማድረግ አረጋግጧል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ሀይል ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ከማግኘት ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር መቻሉን ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ሀይል አመንጭቶና አጓጉዞ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ከፍተኛ የሀይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ መስመሮች ደህንነት መጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ የጸጥታ አካላት ብቻ አይደለም ያሉት ኢንጂነር አሸብር፤ ህብረተሰቡ የሀይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ መስመሮችን ከስርቆት በመከላከል ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።