ቀጥታ፡

የሉአላዊነት ቀን   በቦንጋ ከተማ በድምቀት  እየተከበረ ነው

ቦንጋ ፤ ነሐሴ 3/  2016 (ኢዜአ) ፡-  ጳጉሜን 3  የሉአላዊነት ቀን "ህብር ለሁለንተናዊ ሉአላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  ቦንጋ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው። 

ለሀገር ሰላምና ሉአላዊነት ህይወታቸውን ለገበሩ፣ ደማቸውን ላፈሰሱና አጥንታቸውን ለከሰከሱ የፀጥታ አካላት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነው በዓሉ መከበር የጀመረው።

በዓሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር (ዶ/ር) ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር አቶ አንድነት አሸናፊን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎችና ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎችም በተገኙበት እየተከበረ ነው።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ  ፖሊስ አባላት ወታደራዊ   ትርኢቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

በቀጣይም  የፓናል ውይይትና ሌሎች መርሃ ግብሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

የሉአላዊነት ቀን በዓል በአገር ደረጃ ዛሬ እየተከበረ የሚገኘው በለውጥ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተገዳደሩ ፈተናዎችን በመቋቋም የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማፅናት የተከናወኑ  ሥራዎችን በማሰብ ነው ።

ዛሬ ከቀኑ 6፤00 ሰዓት ላይ ደግሞ  የመንግሥትና በግል ተቋማት ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል ሁሉም ሰው ባለበት ቆሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሚዘምርበት ሥነ-ሥርዓት እንደሚኖር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም