የግብርና ዘርፍ ለኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን ግብዓት በማቅረብ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል -ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ዘርፍ ለኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን ግብዓት በማቅረብ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል -ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 3/2016(ኢዜአ)፦የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብርናው ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ግብዓት በማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ዛሬ ጳጉሜ 3 ቀን 2016 ዓ.ም የሉዓላዊነት ቀን ተብሎ ተሰይሞ “ኀብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንኑ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ሉዓላዊነታችንን ጠብቀን መኖራችን ያኮራናል ብለዋል።
የግዛት ሉዓላዊነት ብቻውን እንደማይቆም ተረድተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፤ሉዓላዊነት ሁለንተናዊ መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።
የምግብ ሉዓላዊነት፣የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት የበጀት ሉዓላዊነት፣ታላቁን የሀገር ሉዓላዊነት በጽናት የሚያቆሙ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
እነዚህን የሉዓላዊነት ዘርፎች ለማስከበር አዲስ ዓይነት ዐርበኝነት ያስፈልገናል ብለዋል።
ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው ኢኮኖሚን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ሲሆን በዚህ ረገድ ግብርናው ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይታወቃል ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብርናው ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ግብዓት በማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
መንግስትም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ምርትና ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ አስቻይ ሪፎርሞች ማካሄዱን ተከትሎ በሁሉም መስክ የምርት እድገት መኖሩን አብራርተዋል ፡፡
የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ማለት በምግብና ስነ ምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግን እንደሚጨምር አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ረገድ ከማምረት ባለፈ ለህብረተሰቡ ተመጣጣኝ ይዘት ያላቸውን ምግቦች ተደራሽ ማድረግ መጀመሩን በበጎ አንስተዋል፡፡
ስንዴና የደጋ አካባቢ ሰብል በክረምት ብቻ ይመረታል የሚለውን አመለካከት በመቀየር በዝናብ አጠርና ቆላማ አካባቢ በመስኖ በማልማት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አስተራረስ ዙርያ ከፍተኛ ለውጦች መኖራቸውን አክለዋል ፡፡
በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ ችግኞች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ መንገዶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው የግብርና ምርቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ፣ ይህን ለማስቀረት ምርትን በብዛት ማምረት ይገባል ብለዋል፡፡
በስንዴ የተገኘውን ተሞክሮ በሌሎች የግብርና ምርቶችና እንስሳት ሃብቶች ላይ በመድገም ከውጭ የሚገባውን ምርት መተካት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ማምጣት እንዲችሉ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ፡፡