ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ሰላምን በማጽናትና ልማትን በማረጋገጥ በጋራ ልንቆም ይገባል 

አዲስ አበባ ፤ጳጉሜን 3/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን  የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ሰላም በማጽናትና ልማትን በማረጋገጥ በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ጳጉሜን 3 የሉዓላዊነት ቀን "ኅብር ለሁለንተናዊ ሉአላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ በመላ አገሪቱ በተለያዩ መርኃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

በአዲስ አበባም ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፌዴራል፣ የከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት አመራሮችና የመዲናዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ ተከብሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በልጆቿ ደምና አጥንት ተጠብቆ የኖረ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን በውድ ዋጋና መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ ሉዓላዊነት ጠብቀንና አስከብረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ልማት የሚረጋገጠው አገር በነጻነት ተከብራ ስትቀጥል በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ እንከፍላለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ውድ ዋጋ እየከፈሉ የሚያጸኗት ጀግኖች ልጆች እንዳሏት በመጥቀስ ለእነዚህ የቁርጥ ቀን ልጆቿ ክብርና ምስጋና ይገባል ብለዋል።

ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን እስካላረጋገጥን ድረስ ሉዓላዊነት ሙሉ አይሆንም ያሉት ከንቲባዋ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እጆቻችንን አበርትተን በትጋት መሥራት ይገባናል ብለዋል።


 

በእልህና በቁጭት በመሥራት በደምና አጥንት ተጠብቆ የቆየውን ነጻነት በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ጭምር ማጽናት እንደሚገባም ነው የገለጹት። 

እንደ አገር ብዙ ዕዳ የተረከብን ቢሆንም ቀን ከሌሊት በመሥራት ለትውልድ ዕዳ ሳይሆን ምንዳ በማስተላለፍ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን እናረጋግጣለን ብለዋል።

ለዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአዲስ አበባ የተሰሩ ሥራዎች ሁነኛ ማሳያ መሆናቸውን አንስተው ይህንን ተባብሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን ትኩረታችንን ዓላማችን ላይ በማድረግ ሰላማችንን በማጽናትና ልማትን በማረጋገጥ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

ሕዝቡ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መጠበቅ ከሰላምና ጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እስከዛሬ ለሰራው ሥራ አመስግነው በቀጣይም ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።


 

የአዲስ አበባ  ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ  ኃላፊ  ሊዲያ ግርማ  በበኩላቸው አገራዊ  አንድነትን በማጠናከር  የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ማህበረሰቡን በማሳተፍ የሰላምና የፀጥታ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ወቅቱ  አንድነትና ኅብረትን የሚጠቅይ መሆኑን በመጠቅስ ሁሉም በመደራጀትና በመሰባሰብ  ከፀጥታ ኃይሉ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።   

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም