ቀጥታ፡

ጎረቤት ሶማሊያውያን የራሳቸው ያልሆነ ጦርነት ወደ ሀገራቸው በመጋበዝ ቀጣናውን ወደ ቀውስ እንዳይከቱ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ ጎረቤት ሶማሊያውያን የራሳቸው ያልሆነ ጦርነት ወደ ሀገራቸው በመጋበዝ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ወደ ቀውስ እንዳይከቱ ሲሉ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች ጥሪ አቀረቡ።

የሀገር ሽማግሌዎቹ እና የህብረተሰብ ተወካዮቹ ጥሪውን ያቀረቡት በአፍሪካ ቀንድ እየተስተዋሉ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመከሩበት ወቅት ነው።

ውይይቱን የመሩት የሶማሌ የሀገር ሽማግሌ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ፥ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ እንደነበረ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ሁሉ የሶማሌ ክልል ህዝብ ጉዳት በመሆኑ፤ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመሆን የሀገርን ጥቅም ለማስከበር መሰራት እንዳለበት በውይይቱ መነሳቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷን ለማረጋገጥ የምትሰራቸውን ስራዎች የሶማሌ ክልል ህዝብ እንደሚደግፍም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

የተለያዩ ሀይሎች ወደ ሶማሊያ መጥተው የአፍሪካ ቀንድን ለማበጣበጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም እንቃወማለን ሲሉ ተናግረዋል።


 

እነዚህ ሀይሎች ለጎረቤት ሶማሊያ ህዝብ ጥቅም የሚያመጡ ሳይሆኑ፣ አዲስ ጦርነት በመክፈት ችግር የመፍጠር ዓላማ ያላቸው መሆናቸውን በመጠቆም ህዝቡ ሊቃወማቸው እንደሚገባም ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ህዝብ እና የሶማሊያ ህዝብ ድንበር ቢለያቸውም ወንድማማቾች ናቸው ያሉት የጎሳ መሪው፤ የአብሮነት ታሪካቸውን ሊጠብቁት ይገባል ብለዋል።

የባህር በር ጥያቄ አብረን የምናድግበት እንጂ የሚያራርቀን አጀንዳ እንዳልሆነ ለጎረቤቶቻችን ሶማሊያውያን ማሳወቅ እንወዳለን ሲሉም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ላለፋት 40 ዓመታት የሶማሊያ ህዝብ ሲቸገር አንድም ቀን አላስታወሱትም፣ ከሽብር ጥቃትም አላዳኑትም ያሉት የጎሳ መሪው፤ ዛሬ ላይም ከአልሻባብ ጋር ለመዋጋት ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ የሶማሊያ ህዝብ ተው ሊላቸው ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብቷን እውን ከማድረግ የትኛውም ኃይል ሊያስቆማት እንደማይገባ የጠቆሙት የሀገር ሽማግሌው፤ የሶማሊያ መንግስትም ውሳኔውን እየተቃወሙ ያሉ ህዝቦቹን ሊያደምጥ ይገባዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለሶማሊያ ባለውለታ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከ500 ሺህ በላይ የሶማሊያ ስደተኞ በኢትዮጵያ መኖራቸውን የጠቀሱት ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ፤ ባለፋት 40 ዓመታትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች መጠለያቸው ኢትዮጵያ ነበረች፤ ሀብት ንብረትም አፍርተዋል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ እና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እየተማሩ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሶማሊያ ህዝብ ውለታ መላሽ ነው ያሉት ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ፤ ጥቂት ግለሰቦች ስልጣንን ተገን በማድረግ ወንድማማች ህዝቦችን ጠላት ለማስመሰል እየሞከሩ ነው፣ ይህ አይሳካላቸውም፣ ህዝባቸውም እየተቃወማቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ህዝቡ አቁሙ፤ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን ጠላት አይደለንም፤ አብረን የማደግ ፍላጎት ነው ያለን እያላቸው ነው፤ ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብና የሶማሊያ ህዝብ ሽብርተኝነትን አብሮ ተዋግተዋል፤ ሰላማችንን የሚያደፈርስ ሌላ ኃይል በመካከላችን ሊገባና ሊጎዳን አይገባም፤ ይህን ሁሉም ሊረዳው ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ኡጋዝ አሊ በበኩላቸው፥ ሶማሊያ ከሩቅ ሀገራት ይልቅ ከጎረቤቶቿ ጋር በመወያየት የሚፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ አግባብ ልትፈታ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ከውጭ የሚመጡ ኃይሎች የኢትዮጵያንና የሶማሊያን ጉርብትና ከማበላሸት ያለፈ ዓላማ አይኖራቸውም ብለዋል።

ወጣቶችና ሴቶችን ወክለው በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎችም፥ ሶማሊያውያን ችግር በገጠማቸው ጊዜያት ሁሉ ቀድማ የምትደርሰው ኢትዮጵያ እንደሆነች ጠቁመው፤ ይህ አጋርነት እንዲቀጥል የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ማለታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ቀንድን በእጅ አዙር ችግር ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ ኃይሎች ዕድል እንዳያገኙ ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም