በክልሉ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቶችን በሪፎርሙ በማስተካከል የተሳለጠና ፍትሃዊ አገልግሎት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ይሰጣል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቶችን በሪፎርሙ በማስተካከል የተሳለጠና ፍትሃዊ አገልግሎት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ይሰጣል
ባህር ዳር/ደብረ ብርሃን/ደሴ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቶችን በሪፎርሙ በማስተካከል የተሳለጠና ፍትሃዊ አገልግሎት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ እንደሚሰጥ ተገለፀ።
በክልሉ በባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃንና ደሴ ከተሞች የሪፎርም ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከንቲባው የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሞላ ሁሴን እንደገለጹት፤ በአዲሱ ዓመት የከተማዋን ህዝብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች የማረም ተግባር በትኩረት ይከናወናል።
የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የሪፎርም ተግባራት በላቀ አፈፃፀም እንደሚከናወኑም ገልፀዋል።
ለዚህም የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ቀልጣፋና ፍትሃዊ መስተንግዶ እውን እንዲሆን በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ግንባር ቀደም ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ሲቪል ሰርፊስ መምሪያ ሃላፊ አቶ ጤናው ምህረቱ በበኩላቸው፤ በአዲሱ በጀት ዓመት የሲቪል ሰርቫንቱን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመለየትና ክፍተቶችን የማስተካከል ስራ ይከናወናል።
የተገልጋዩ ህብረተሰብ የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ በእውቀትና ክህሎት የዳበረ እንዲሁም ስራውን በሃላፊነት የሚከውን ሲቪል ሰርቫንት በመገንባት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተለይም በተቋምት የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት በቴክኖሎጂ በታገዘ አግባብ በማስተካከል እርካታን የሚያረጋግጥ አገልግሎት ተደራሽ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቶችን በሪፎርሙ በማስተካከል የተሳለጠና ፍትሃዊ ግልጋሎት ህብርተሰቡ እንዲያገኝ ይደረጋል ያሉት ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን የዋና አስተዳዳሪው የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ዓይነኩሉ አበበ ናቸው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ስራዎች ጎን ለጎን የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በለውጡ ዓመታት የህዝቡን የተገልጋይነት እርካታ ለማሳደግ የሪፎርም ስረዎች መሰራታቸውን አስታውሰው፤ የተገልጋይን እርካታን በማረጋገጥ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ገልፀዋል።
በመሆኑም 2017 ዓም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የላቀ የሰው ሀይል በመገንባት ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አበበ በበኩላቸው፤ በ2017 ዓ/ም ጥራት ያለው አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት የመረጃ አያያዝን የማዘመን ስራ ይከናወናል።
በሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንዲሁም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን በማጥራት ጭምር የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለመፍታት በተቀናጀ አግባብ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የሪፎርም ቀን ስናከብር ለቀጣይ ተግባራትና ተልዕኮዎች የምንተጋበት በመሆኑ ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ለላቀ የህዝብ አገልግሎት መነሳሳት እንዳለበት አሳስበዋል።
ዻጉሜ 2 ቀን ''ለላቀ አገልግሎት“ በሚል መሪ ሀሳብ ሲከበርም የመንግስት የስራ ሀሃላፊዎችና ባለድርሸአ ካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር የሪፎርም ቀንን "ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት" በሚል መሪ ሀሳብ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን በዛብህ እንደገለፁት፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
በዚህም ተግባራዊ የተደረገውን የሪፎርም ማሻሻያ በመጠቀም ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት መስጠት እንደተቻለ ገልፀዋል።
ሪፎርሙ ወጭ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት፣ ተቋማትና ሙያተኞች ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ ማስቻሉን አመልክተው፤ ሰራተኞች የተቀራረበ አፈፃፀም እንዲኖራቸው፣ ግልፅ እቅድ እንዲያወጡና በአፈፃፀሙ ተጠያቂነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማስቻሉንም አስገንዝበዋል።
እንዲሁም ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከልና በአገልግሎት አሰጣጡ ዘርፍ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን ለማቃለልም እንዳገዘ ተናግረዋል።
ቀጣይ በአዲሱ ዓመትም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የከተማውን ሁለተናዊ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ ካሳው በበኩላቸው፤ በስማርት ሲቲ አሰራር አገልግሎት አሰጣጡን ከማሻሻል ባለፈ የከተማውን ሀብት በአግባቡ ለመያዝና ለመጠቀም አስችሏል።
የሪፎርም አሰራሮች ከተማውን ዲጅታላይዝድ የማድረግ ሥራ መጀመሩንና በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
ለስራ እድል ፈጠራ፣ ገቢ አሰባሰብ፣ የከተማ መሬት ካዳስተር በማዘመንና በሌሎች የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮችን ለማሻሻል በአዲሱ ዓመት በልዩ ትኩረት እንደሚፈፀም አብራርተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማው ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ የሱፍ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በጤናው ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሕዝቡን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ተችሏል።