ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቻይና ኢንቨስመንት እና የልማት ትብብር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ መጥቷል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ቻይና ኢንቨስመንት እና የልማት ትብብር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ መምጣቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው ቻይናዊ ፕሮፌሰር ዋንግ ዢንግፒንግ ገለጹ።

እ.አ.አ በ1970ዎቹ መባቻ የጀመረው የኢትዮጵያ እና ቻይና ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመንግስታት መለዋወጥ ሳይዋዥቅ በየጊዜው እየላቀ የመጣ ጠንካራ ወዳጅነት ነው።

በወቅቱ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እና የኮሙኒስት ቻይና መስራቹ ማኦ ዜዶንግ መካከል የተደረገው የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚና ቴክኒክ ትብብር ስምምነት ጀምሮ ዛሬም ሁለንተናዊ ትብብሮች ቀጥለዋል።

በተለይም ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የቻይና-አፍሪካ ትብብር ጉባዔ ከተጀመረ ወዲህ የሁለቱ ሀገራት አጋርነት እና የትብብር መስኮች እየሰፉ መምጣታቸው ይጠቀሳል።

ሁለቱ ሀገራት ከጥቅምት 2016 ዓ.ም ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ በሁሉም ሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ከፍ ማድርጋቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በታደሙበት ሰሞነኛው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ጉባኤም፥ ኢትዮጵያና ቻይና 17 የመግባቢያ ሰነዶች መፈራረማቸው ተገልጿል።

በቻይናው ሳውዝኢስት ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰሩ ዋንግ ዢንግፒንግ፤ የኢትዮ-ቻይና የልማት ትብብር እና ኢንቨስመንት ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ መቀጠሉን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያና በተቀረው አፍሪካ በግንባታው፣ በኢንዱስትሪና በተለያዩ ኢንቨስመንት ዘርፎች በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲጎለብት የራሳቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ያነሳሉ።

በኢንዱስትሪዎች በኩል የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድም ውጤታማ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በዘንድሮው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ጉባዔ የቻይናው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ሀገራትን በልማትና ሌሎች መስኮች ለመደገፍ አዲስ ኤኒሸቲቭ ይፋ ማድረጋቸው ትብብሩን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና በተለይም በትምህርት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ቢያጠናክሩ በሰው ኃይል ግንባታ ላይ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም