ቀጥታ፡

በክልሉ የወጡ የህግ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች ለአገልግሎት አሰጣጡ መሳለጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተገለፀ 

ባህር ዳር ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦  በአማራ ክልል ለውጡን ተከትሎ የወጡ የህግ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች ለአገልግሎት አሰጣጥ መሳለጥ ቁልፍ ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሀመድ (ዶክተር )ገለፁ።

"ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ የሪፎርም ቀን በፓናል ውይይት በባህር ዳር ከተማ ተከብሯል።

ቢሮ ሃላፊው አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ አገር አቀፍ ለውጡን ተከትሎ በየዘርፉ የወጡ የህግ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች ለአገልግሎት አሰጣጥ መቀላጠፍ የላቀ ሚና አበርክተዋል።

በተለይ ከዲጂታላይዜሽንና ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የተዘረጉ የአሰራር ስርዓቶችን ለማቃለልና ለማቀላጠፍ የወጡ ፖሊሲዎችና የህግ ማዕቀፎች ፋይዳቸው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለዚህም በሁሉም ተቋማት ከሰው ኃይል እስከ ቴክኖሎጂ ድረስ በተካሄዱ ሪፎርሞች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።

በተለይ ምቹ የስራ ካባቢን ለመፍጠር የተደረጉ ሪፎርሞችና የአሰራር ስርዓቶች በቀጣይም እስከታችኛው የአስተዳደር ዕርከን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

ለአገልግሎቱ መሳለጥ የወጡ የህግ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎችን ተከትሎ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለማረም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በዲጅታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ በተሻለ አግባብ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያም ለላቀ አገልግሎት ራሱን ሊያዘጋጅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽነር ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረ ማርያም እንዳሉት፤ አገልግሎትን ለተገልጋዩ ህብረተሰብ በቅንነትና በታማኝነት መስጠት ተገቢ ነው።


 

በዚህም መልካም ስነ-ምግባር ያላቸው ታታሪ ሰራተኞች እንዳሉ ሁሉ አገልግሎትን የሚያጓድሉ ችግር የሚስተዋልባቸው ሰራተኞች እንዳሉም ተመላክቷል።

ህብረተሰቡ በየመድረኩ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማስወገድ፣ ታማኝና ቅን አገልጋይ ሰራተኛ ለመፍጠር የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ፖሊሲ ፀድቆ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ለህብረተሰቡ በቅንነትና ታማኝነት አገልግሎትን በመስጠት በኩል ያሉትን ክፍተቶች ለማረምና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የአጫጭርና የረጅም ጊዜ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በመስጠት የማብቃት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

''የአገልግሎት አሰራር ችግሮችን ለማስወገድና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ ሰፊ የህግ ማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ነው'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም ናቸው።


 

ህብረተሰቡም ለፍትህ ስርዓቱ ፈተና የሆነውን ሀሰተኛ ምስክር ለማስቀረት እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ የፍትህ ስርዓቱን ዳር እንዲደርስ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት’’ በሚል በተዘጋጀው መድረክ የክልሉ አመራር አባላት፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም